በጋምቤላ ክልል በብልጽግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ
በጋምቤላ ክልል በብልጽግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በጋምቤላ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፓርቲው አካታችነት ያለው አሰራር በመተግበር ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ማሳተፍ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በተለይም እንደ ጋምቤላ ክልል የልማት አቅሞች የተለዩበትና ድሎች የተመዘገቡበት እንደሆነም ተናግረዋል።
እንደ ክልል በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስታችን ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ በነበሩት 5 ዓመታት ለህዝባችን ቃል በገባነው መሠረት አመራሩንና ህዝቡን በማስተባበር በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል።
የማዕድን ዘርፉ አንዱ የዕድገት ተኮር ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ትላልቅ የወርቅ አምራች ኩባንያዎችን ሳይጨምር ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ለብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ከነበረበት122.24 ኪሎ ግራም ወደ 5 ሺህ 429 ኪሎ ግራም የተጣራ ወርቅ በማሳደግ ለአገር ልማት ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች ዘርፎችም እመርታዊ ለውጦች በማስመዝገብ የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ አጋርነትን በማስቀረት እኩል ውሳኔ ሰጭነትን ተግባራዊ ያደረገ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በየደረጃው ውጤታማ ስራዎች እየሰራ መምጣቱን ገልፀው የራሰን አቅም በማሳደግና ልማትን በማረጋገጥ ተጠቃሚነትን ያስገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በህዝብ ድጋፍና ምርጫ ወደ መሪነት የመጣው ፓርቲው በየደረጃው የሚገኘውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገቶች በማስመዝገብ ሀገራችንን ወደ ብርሃን አሸጋግሯል ሲሉም ገልጸዋል ።
ዘንድሮ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ብልፅግናን መምረጥ የተመዘገቡ የልማት ድሎችን ማሰቀጠልና ውጥኖችን ግብ ማድረስ እንደሆነም አቶ አሽኔ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ የክልሉ የፓርቲና መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።