በቦንጋ ከተማ አስተዳደር ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚደረገው የአደባባይ ላይ የቅስቀሳ መርሃ ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዛሬው ዕለትም የኮሌጅ ፣ የሸታ እና የዩኒቨርሲቲ ቀጠና ነዋሪዎች አደባባይ ላይ በመውጣት ለብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።
በአደባባይ ድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት የቦንጋ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተክለአብ ቡሎ ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ለወጡ ነዋሪዎች ምስጋናቸውን በማቅረብ ሀገራችን ለረጅም ጊዜ በቁርሾ ፖለቲካ እና በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፏን አስታውሰው አሁን ያለው ትውልድ በትከሻው የተጣለውን የሀገር ኃላፊነት በመወጣት ነገን የተሻለ ለማድረግ ቆርጠው መነሳቱን ገልጸዋል።
ትውልዱ ከየትችት ፖለቲካ ወጥተው በተስፋ የሚሻገርበትን ራዕይ መከተል እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዶ/ር ተክለአብ አክለውም፣ እንደ ሀገር ያሉብን ችግሮችና እዳዎች በርካታ ቢሆኑም በመደጋገፍና ክፍተቶችን በመሙላት ላይ ካተኮርን ለነገ የሚሻገር ታሪክ መጻፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ግብ ሰርተው በማጠናቀቅ ነገን እዳ የሌለባት ሀገር ለትውልድ ማስረከብ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጹን ለብልጽግና ፓርቲ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በሀገርና በክልል ደረጃ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ በከተማዋ በብዙ ሚሊዮኖች የተገነቡ ፕሮጀክቶች የሚመረቁበትና አዳዲስ ስራዎች የሚጀመሩበት ወቅት መቃረቡን በምሳሌነት አንስተዋል።
በሌላ በኩል የከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍሬው አበበ ፓርቲው ባለፉት ስምንት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በቦንጋ ከተማ ያመጣቸውን ሁለንተናዊ ለውጦች በዝርዝር አብራርተዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ሁሉንም ክልሎችና ዜጎችን በውሳኔ ሰጪነት ላይ ያሳተፈ አካሄድ መከተሉንና በኢኮኖሚው ረገድም የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም በቦንጋ ከተማ የሚታዩ የኮሪደር ልማቶች ፣ የስማርት ፖሎች ተከላና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ የፓርኮች ግንባታ የፓርቲው የልማት ተነሳሽነት ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲ ቀጠና እየተገነቡ ያሉ የኢንቨስትመንት ማዕከላት ፣ የአየር ማረፊያ ግንባታና የግብርና ኮርፖሬሽን ስራዎች ለነዋሪው ሰፊ የስራ እድልና የኢኮኖሚ መነቃቃት እየፈጠሩ መሆኑን አቶ ፍሬው አስረድተዋል።
ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠልና የተሻለች ነገን ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን በማስገንዘብ ፣ መላው የከተማዋ ነዋሪ ከፓርቲው ጎን እንዲቆም ጥሪ አማቅርበዋል።