Prosperity Party

ሳምንታዊ መልዕክት

በሀገራዊ ለውጡ የጀመርነውን የእውነተኛ ዴሞክራሲ ባህል ግንባታ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እናሸጋግረዋለን

ፓርቲያችን ብልፅግና በሀገራዊ ለውጡ ከተረከባቸው ተልዕኮዎች መካከል እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ስልጡን የፖለቲካ ባህል ግንባታ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ እርምጃዎች በሀገራችን ታሪክ በተለይ ደግሞ በዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ለረጅም ጊዜ ይስተዋል የነበረውን የኃይል ፖለቲካ በሰለጠነ የሀሳብና የምክክር ፖለቲካ ለመተካት አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የተቻለባቸው ነበሩ፡፡ ለውጦቹ ለዘመናት ከመጣንበት እና ተጣብቶብን ከቆየው ኋላቀር የፖለቲካ ባህል አንጻር ፈታኝ የነበሩ ቢሆኑም በተደረጉ ተከታታይ ሪፎሞች እና በተሰሩ የተቋም ግንባታ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ፍሬ ማፍራት እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል፡፡

ሀገራዊ ለውጡ በቅድሚያ ካስተካከላቸው ችግሮች ቀዳሚው የነበረብንን የሀሳብ ስብራት መጠገን አንዱና ዋነኛው ሲሆን ለዚህም የመደመር ዕሳቤ እንደ ፍቱን መድኃኒት ተቀምሮ አጠቃላይ ሪፎርሙ የሚመራበት የዕሳቤ ማዕቀፍ በመሆን እንዲያገለግል ተደርል፡፡ በመደመር ዕሳቤና መንገድ አጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ በትብብርና ፉክክር መካከል ሚዛን እንዲኖር፣ አቃፊነትና አሳታፊነት እንዲዳብር ተደርል፡፡ በዕሳቤ ደረጃ የመጣውን ለውጥ ህጋዊነትና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ተቋማትን በህግና በአሠራር የማሻሻልና የመገንባት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል እንደ ምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያና የሲቪል ማህበረሰብ ያሉ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም የፍትህና የጸጥታ ተቋማት የሚጠቀሱ ሲሆን እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሉ አዳዲስ ተቋማት ደግሞ የዘመነ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ጥረታችንን በግዝፈቱ ልክ ወደ ፊት እንዲራመድ ለማስቻል ታስበው የተፈጠሩ ናቸው፡፡

ፓርቲያችን ብልፅግናም በሀገራዊ ሪፎርም ሂደቱ ውስጥ ከተመሰረቱ ተቋማት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ቀደም ብሎ የነበረውን ኢትዮጵያን በልዩነቶች ብቻ የሚከፋፍል የፖለቲካ አስተሳሰብ በማረም ከሁሉም ለሁሉም በሁሉም የሆነ ወጥ፣ አቃፊና አካታች ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ እንዲወጣ ተደርል፡፡ ይህ ለውጥን ከራስና ከውስጥ የመጀመር ተግባር ደግሞ አጠቃላይ ሪፎርሙ በአስተማማኝነት ወደ ፊት እንዲገስግስ ጉልህ እገዛ አበርክቷል፡፡

አጠቃላይ የሀገራዊ ለውጡ ግስጋሴ ሁለት ዋና ዋና ምዕራፎች አሉት፤ እነዚህም 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ናቸው፡፡ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተጠነሰሰው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ፖለቲካችንን የማዘመን ጅማሮ በመንግሥት፣ በህዝብ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች ከፍተኛ ትብብር እና ቁርጠኝነት ታጅቦ በጋራ ድል የተጠናቀቀ ምዕራፍ ነበር፡፡ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ደግሞ ከዚያ በበለጠ ትብብርና ቁርጠኝነት የእውነተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዟችንን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ይህ ሁኔታ ፓርቲያችን በሪፎርሙ መነሻ ላይ ለህዝብ የገባውን ቃል አክብሮ በተግባር እያሳየ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ህዝብና የሀገራችን የፖለቲካ ተዋንያንም የብልፅግና ፓርቲን ተነሳሽነትና ተግባራዊ እርምጃ በተለያየ መንገድ እያጠናከሩና እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ ፓርቲያችን ብልፅግናም ያነገበውን እና ከህዝብ በአደራ የተቀበለውን የሠለጠነ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ተልዕኮውን ከዳር ለማድረስ የታደሰ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ያለው መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ

መጋቢት 14፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party