ሳምንታዊ መልዕክት
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሴቶች ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላችውን ሚና ጎልቶ የሚታይበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው፤
ሴቶች የቤተሰብ እና የሀገር መሠረት ናቸው፡፡ ይሁንና እነዚህ የቤተሰብና የሀገር መሠረት የሆኑት እንዲሁም የህዝባችንን ግማሽ ቁጥር የሚይዙት ሴቶች ባለፉት ዘመናት ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ትርጉም ባለው መልኩ ሲከበር አልተስተዋለም፡፡ ሀገራዊ ለውጡ ይህንን ማህበረሰባዊ ጉድለት በአግባቡ በመገምገም አያሌ የመፍትሄ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል የሴቶችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ሥራዎች እስከ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በሴቶች እንዲመሩ ማስቻል የዘለቁ ታሪካዊ ውሳኔዎችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የለውጥ መንግሥት በሰው ተኮር ሥራዎቹ አማካይነት የሴቶችን ለችግር ተጋላጭነት የሚቀንሱ አያሌ የማህበራዊ ፕሮግራሞችን ሲተግበር ቆይቷል፡፡ በጤና፣ በትምህርት፣ በሥራ ዕድልና ፈጠራ፣ በመኖሪያ ቤት ዕድሳትና ግንባታ፣ በፋይናንስ ተደራሽነት የመሳሰሉ ማህበራዊ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቶ በሴቶች፣ በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ህይወት ውስጥ በርካታ መሻሻሎችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በከፋ ህይወት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሴቶች ዘመናዊ የማገገሚያ ማዕከላት በመገንባት ከችግር እንዲወጡና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አያሌ የምገባ ማዕከላት በመገንባት የዕለት ጉርስ የሚቸገሩ ዜጎች የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ህጻናት ተማሪዎች በቂ ምግብ እያገኙ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በየቀኑ ያልተቋረጠ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ለቅድመ-መደበኛ ትምህርት የተለየ ትኩረት በመሥጠት ከ30ሺ በላይ የቅድመ-መደበኛ ት/ት ቤቶች በመገንባት ነገ በብቃት ሀገር የሚረከቡ ኢትዮጵያዊያን ልጆች እንዲኖሩ ትውልድን ማዕከል ያደረገ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ማህበራዊ ዋስትናን ከሚያረጋግጡ እና በግንባር ቀደምነት ሴቶችን ተጠቃሚ ከሚያደርጉ ሰው ተኮር ሥራዎች ጎን ለጎን የሴቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለሀገር ግንባታ ለመጠቀም የሴቶችን መሪነት ያረጋገጡ በታሪክ ታይተው የማይታውቁ አዳዲስ ለውጦች ተፈጥረዋል፡፡ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የለውጥ መንግሥት የሚንስትሮች ምክር ቤት 50 በመቶ በሴቶች እንዲያዝ ማድረግን ጨምሮ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት የሴቶች የአመራር ተሳትፎ ከፍ እንዲል አድርጓል። በዚሀም በሀገራችን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ፋና ወጊ የመንግሥት አስተዳደር ሪከርድ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ከዚህ በፊት በተለምዶ ለሴቶች የማይሰጡ ተደርገው ሲሳሉ የቆዩ የኃላፊነት ቦታዎችን ጭምር ሴቶች እንዲይዟቸው በማድርግ ሴቶች በትላልቅና ቁልፍ የአመራር ቦታዎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በተግባር አሳይቷል። በዚህ መሠረት በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ርዕሰ ብሔር፣ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣ ሴት መከላከያ ሚንስትር፣ ሴት አፈ ጉባኤ፣ ሴት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ ሴት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ፣ ሴት የክልል ፕሬዚደንት፣ ሴት የዞን አስተዳዳሪዎች ወዘተ ማየት ችለናል፡፡
ይህ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያደገበት ታሪካዊ ክስተት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እጅግ ያስፈልጋል፡፡ ፓርቲያችን ብልፅግናም የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ከዚህም በላይ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከምን ግዜውም በላይ ቁርጠኛ ነው፡፡ ይህንን ለማስቻል ደግሞ ምርጫ ቁልፍ ምዕራፍ ነው፡፡ ስለሆነም ሴቶች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ በመራጭነት ጨምሮ በሁሉም የምርጫው ሂደቶች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ሚና አጉልተው እንዲያሳዩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚም በድጋሜ እንኳን ለዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን አደረሳቹ አደረሰን ለማለት እንወዳለን!
ብልፅግና ፓርቲ
የካቲት 30፤ 2018 ዓ/ም