ሳምንታዊ መልዕክት
አያቶቻችን በመስዋዕትነታቸው ያቆዩልንን ሀገር ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥትን በማፅናት እናስቀጥላለን፤
እንኳን ለ130ኛ የዓድዋ ድል በዓል አደረሰን!
ታላቁ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ህብረ-ብሄራዊ አንድነት ተምሳሌት ነው፡፡ ድሉ ኢትዮጵያዊያን በመደመር ስሜት ስንሰባሰብ ምን አይነት ገድል መፈጸም እንደምንችል ያስመሰከርንበት እና ይህንኑን ለዓለም ያንጸባረቅንበት የአኩሪ ታሪካችን ቁንጮ ነው፡፡ የዓድዋ ድል በጊዜው የገጠመንን የቅኝ ግዛት አደጋ በጋራ ተሰልፈን የቀለበስንበት አስደማሚ ታሪካችን ነው፡፡ ድሉ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የሚኖሩንን ተስፋዎች ማስቀጠል እንደምንችል እንዲሁም የሚገጥሙንን ፈተኛዎች በድል እንድንወጣቸው የማይነጥፍ ስንቅ ሆኖ ሲያገለግለን ቆይቷል፤ አሁንም እያገለገለን ይገኛል፡፡
በዚህ ዘመን የሰነቅነውን የብልፅግና ዓላማ ወደሚጨበጥ ተስፋ ማሸጋገር የቻልነውም በዚሁ በመደመር ዕሳቤና በዓድዋ ድል ስሜት ነው፡፡ እንደ ነጠላ ትርክትና ፅንፈኝነት ያሉ የሚገጥሙን ፈተኛዎችም በተመሳሳይ መንገድ እየተሻገርን ብሎም ፈተናን ወደ ዕድል እየቀየርን ኢትዮጵያን ተምሳሌታዊት ሀገር ለማድረግ ጉዟችንን አጠናክረን ቀጥለናል፡፡ በተለይ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደታችን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ በተሸጋገረበት በዚህ ወቅት የነጠላ ትርክትና ፅንፈኝነት ፈተናዎች ከማንኛውም ጊዜ በላይ የምንታገለውና ድል የምንነሳው ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ድል የዘመናችንን አርበኝነት የሚጠይቅ በወልና ብሔራዊ ትርክት ጋሻዎች የምንመክተው የዓድዋ ድል ቀጣይ ምዕራፍ ነው፡፡
ፓርቲያችን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያነገባቸውን መንትያ ግቦች ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ምርጫው በአንድ በኩል ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሚያስችሉ አያሌ ሥራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በሌላ በኩል ፓርቲያችን ብልፅግና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ በመቅረብ ህዝባዊና ህጋዊ መንግሥት ሆኖ ለመቀጠል ሰፋፊ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
የዓድዋ ድል ነጻነቷን ፣ ክብሯ እና ማንነቷን የጠበቀች ሀገር እንድትኖረን እንዳስቻለን ሁሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ሉአላዊነቷ የተከበረ እና ህጋዊና ህዝባዊ መንግሥት ያላት ሀገር ሆና እንድትቀጥል የማድረግ አስፈላጊነት ከፍ ያለበት የጋራ ብሔራዊ አጀንዳችን ነው፡፡ ለዚህ ብሔራዊ አጀንዳ መሳካትም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዳሳየነው እና በያዝነው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እስካሁን እንዳሳካነው የሁላችንም ቀጣይ ተሳትፎና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንኑን በማድረግ አያቶቻችን በመስዋዕትነታቸው ያቆዩልንን ሀገር ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት በማፅናት ማስቀጠል ይገባናል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
የካቲት 23፤ 2018 ዓ/ም