ሳምንታዊ መልዕክት የቱሪዝም ዘርፍ እመርታችን የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ፤ የአፍሪካ ተምሳሌትነት ጉዞ መስፈንጠሪያ ነዉ
የመደመር ዕሳቤ እየፈጠራቸው ካሉ እመርታዎች አንዱና ዋነኛው ኢኮኖሚያችን ብዝሀ ዘርፍ፣ ብዝሀ ተዋናይ እና ብዝሀ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ለዘመናት ከቆየበት የግብርና ነጠላ-ዘርፍ ወደ ብዝሀ-ዘርፍ ለማሸጋገር አያሌ የፖሊሲ ጥናቶችንና ውሳኔዎችን ጠይቋል፤ ከዚህ በፊት ያልታየ የዕሳቤ ለውጥ እና የመንግሥት ቁርጠኝነት አስፈልጓል፡፡ የኢኮኖሚያችን እምቅ አቅም በተደመረና በተሰናሰነ አግባብ ለመጠቀም በተደረገ በዚህ ጥረት ኢኮኖሚያችን ከአንድ ዘርፍ ወደ አምስት ዘርፎች ወይም አምዶች እንዲያድግ ተደርጓል፤ እነዚህም ግብርና፣ አምራች እንዱስትሪ፣ ማዓድን፣ ቱሪዝም እና አይሲቲ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚው ተዋናንያን ከመንግሥት ብቸኛና ገናና ተዋናይነት ወደ ግል ዘርፍ እና ወደ ህዝብ እንዲሸጋገር እየተደረገ ይገኛል፡፡ ሽግግሩ አስተማማኝ ለማድረግ ባለሶስት ማዓዝን የትብብር ማዕቀፍ ማለትም የመንግስት-የግል-የህዝብ ማዕቀፍ በመፍጠር ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከተጠቃሚነት አንጻር ከዚህ በፊት የነበረው የተዛባና ኢ-ፍትሀዊ የሆነ ጥቂቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በመግራት ወደ ብዝሀ-ተጠቃሚነት በመለወጥ የህዝብ የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ አዲስ የአኮኖሚ ሥርዓት እዉን ሆኗል፡፡
ከአምስቱ የኢኮኖሚ አምዶች አንዱ ሆኖ እንዲወጣ በተደረገው የቱሪዝም ዘርፍ እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች የኢትዮጵያ የቱሪዝም አቅም በአግባቡ በመገንዘብ የጀመረ ነበር፡፡ ክቡር የፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ “የቱሪዝም ሀብታችን ላይ ያለውን አቧራ አራግፈን አሻራ እናኖራለን” ባሉት መሰረት ዘርፉ ለብሶት የቆየዉን አቧራ ተራግፎ በአሻራ ደምቆ ለመታየት ጀምሯል፡፡ የቆዩ የቱሪስት መስህቦቻችን እየታደሱ ለሀገር ወስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ሳቢና ምቹ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ አያሌ አዳዲስ መስህቦች ተፈጥረው የብዙዎች ቀልብ መሳቢያ ሆነዋል፡፡ ከሁለም በላይ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ የቆየው የተዛባ የትርክትና የትኩረት ችግር በማስተካከል በኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም አቅሞች በእኩል እንዲለሙ እና ጎልተው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡
ይህ እመርታ እዉን መሆን የቻለው መሰረታዊ የሆነው የእሳቤና የእይታ ለውጥ ማድረግ ስለተቻለ ነው፡፡ የመደመር እሳቤ ወደ መሬት ወርዶ እየተተገበረና ከተጠበቀው በላይ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፡፡ በቀጣይነትም ይህ ኢትዮጵያን እየለወጠ ያለው ሀገር በቀል እሳቤ የአፍሪካ የለውጥ ቅያሽ እንዲሆን ራዕይ ተሰንቋል፡፡ በዚህ ራዕይ ውስጥም እንደ ከዚህ ቀደሙ የህዝብ እና የአፍሪካውያን ወንድም-እህቶቻችን ድጋፍ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአርባምንጭ የኮንፈረንስ ሪዞርት ምረቃ መርሀግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ቱሪዝም አዲሱ የአኮኖሚ ምሶሶ መሆኑ እና የቱሪዝም ለውጡ የአፍሪካ ምሳሌ መሆኑ ገልጸዋል፤ ቢሆንም “ምሳሌ” ማለት “ፍጻሜ” ማለት ስላልሆነ በሰራነው ሳንዘናጋ ለቀጣይ ውጤት እንዳዲስ መነሳት ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ከአፍሪካ ማንሰራራት ጋር አቆራኝነት ካላየን ግንጥል ጌጥ ስለሚሆን ጌጣችን ድርብ-ድርብርብ እንዲሆን እንትጋ፡፡
ብልፅግና ፓርቲ
ሰኔ 29፤ 2018 ዓ/ም