መደመር - በሀገር በቀል አቅምና እውነት ላይ የተገነባ አዲስ ዕይታ
የለውጡ መንግሥት ላለፉት ዓመታት ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር "መደመር" የተሰኘውን አገር በቀል ዕሳቤ እንደ ዋነኛ መሪ መርህ በመጠቀም ላይ ይገኛል።
መደመር በባሕርይው ቀደምት ስህተቶችን የሚያርም፣ የነበሩ መልካም እሴቶችን የሚያስቀጥልና የወደፊት አዳዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር የለውጥ መነጽር ነው። ይህ ዕሳቤ "ወርቃማውን አማካይ" በመፈለግ፣ ሀገራችን ለዘመናት ሲያደማ የነበረውን "እኛ እና እነሱ" የሚል የጎራ ፖለቲካና መፈራረጅ በአካታችነትና በአንድነት ለመተካት ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ዘመናት የተከተለቻቸውና ከውጭ የተኮረጁ እንደ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ያሉ ርዕዮተ-ዓለሞች ከትርፋቸው ይልቅ ኪሳራቸው ያመዘነ ነበር ። መደመር እነዚህን ባዕድና ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የማይመጥኑ እሳቤዎችን በመተው፣ በራስ አቅምና እውነት ላይ የተመሠረተ አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመዘርጋት መሠረት ሆኗል።
በዚህ ዕሳቤ አማካኝነት ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል በግብርናው ዘርፍ የታየው "የስንዴ አብዮት" ተጠቃሽ ነው። ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዢ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ የነበረበትን ታሪክ በመቀየር፣ በመስኖ ልማት ራሷን ችላ ምርቷን ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ የመደመር ፍልስፍና በተግባር የታየበት ውጤት ነው።
በተጨማሪ፣ መንግሥት በቴክኖሎጂና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ የአፍሪካ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በማቋቋምና የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) አሰጣጥን በማስፋፋት አገሪቱን ከዘመኑ ጋር ለማላመድ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ከፖለቲካዊ አቅጣጫ አንጻር፣ መደመር ቀደም ሲል "አጋር" ተብለው ከውሳኔ ሰጪነት ተገልለው የነበሩ ክልሎችን ወደ መሀል በማምጣትና የሁሉንም ዜጎች ድምፅ እኩል በማድመጥ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ይህ አካታችነት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ፣ እንደ "አረንጓዴ አሻራ" እና "ገበታ ለሀገር" ባሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ ሕዝቡ በራሱ ፈቃድና አቅም እንዲሳተፍ አነቃቅቷል። ይህም ሁለንተናዊ ብልፅግና ከቁሳዊ ዕድገት ባለፈ፣ የዜጎችን ሥነ-ልቦናዊና መንፈሳዊ እርካታ ያካተተ መሆን እንዳለበት ያሳያል።
የመደመር ዕሳቤ ኢትዮጵያን ከመከፋፈል ወደ አንድነት፣ ከልመና ወደ ራስን መቻል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያሸጋግር ፍቱን መፍትሔ መሆኑን በተጨባጭ ተግባራት የታየ ነው።
በቀጣይም የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በማጠናቀቅና አዳዲስ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና የበለፀገች አገር ለማድረግ የተነደፈው ፍኖተ-ካርታ በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ይሳካል።
መደመር ካለን ነገር ላይ የተሻለውን ወስደን፣ ጎጂውን ጥለን፣ አዲስ ነገር በመጨመር ነገን የተሻለ የማድረግ ጥበብ ሆኖ ይቀጥላል።
#Prosperity