በኢትዮጵያ የፉክክርና የምክክር ሚዛኑን የጠበቀ ጤናማና የዳበረ የፖለቲካ ምህዳር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለፁ።
የአማራ ክልል መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛል።
አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንደገለጹት፥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ በምክክርና በፉክክር ላይ መሰረት ያደረገ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት እየተገነባ ይገኛል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ጠንካራ ህገ መንግስት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የህግ ማዕቀፎች፣ተቋማዊ አደረጃጀቶችና ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ገልፀዋል።
እንዲሁም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ አማራጭ ሀሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ የሚያደርሱበት ምህዳር መመቻቸቱንም አክለዋል።
በተጨማሪም እርስ በእርሳቸው የሚመካከሩበት የሚወያዩበትና የሚነጋገሩበት እንዲሁም ገዥውን ፓርቲ የሚሞግቱበት አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ፓርቲዎች ህግና ስርዓት አክብረው የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር እና ለሰላምና መረጋጋት መስፈን መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል ፅንፈኛ ቡድኖች በህዝብ ላይ እያደረሱ ያለውን በደል ለማስቆምም ፓርቲዎች በትብብር በመስራት ለዳበረ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በሀገራችን የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ ለዳበረ የፖለቲካ ልምምድ ሰላማዊ አማራጭን በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አዎንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ በኋላ ቀር አካሄድ የፖለቲካ ስልጣንን በሀይል ለመያዝ ፋላጎቱ ያላቸው ፅንፈኛ ቡድኖች በክልሉ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ የሚስተዋለውን ችግር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሰለጠነ አግባብ በመነጋገር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ሁሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።