Prosperity Party

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በሁሉም ዘርፎች ለመድገም በቁርጠኝነት ይሰራል - አደም ፋራህ

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በሁሉም የልማት ዘርፎች ለመድገም፣ ሕዝቡን በሰፊው በማሳተፍና የልማት ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ፣ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፣ ሚኒስትሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የፀጥታ ኃይሎችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ህዳሴ ፓርክ በመገኘት አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በዚሁ ወቅት "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል የተካሄደውን የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብር በይፋ ያስጀመሩት አቶ አደም፣ ይህ ቀን ያለ ልዩነት በአንድነት የምንንቀሳቀስበትና የሀገራችንን ታሪክ በጋራ የምንጽፍበት የሀገራዊ አንድነት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

"ባለፈው ዓመት 714 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድነት ተክለናል፤ ዘንድሮ 800 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ትልቅ ሀገራዊ አደራ ነው" ያሉት አቶ አደም፣ ሁሉም ዜጎች አሻራቸውን በማሳረፍ የዚህን ሀገራዊ ግብ እንዲያሳኩ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ2011 ዓ.ም ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆተውን ሥነ ምህዳር ከመመለስ ባለፈ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የታለመ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው።

አክለውም የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንቅፋት ሆኖ ከቆዩ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል የደን መመናመንና በቂ የዛፍ ተከላ አለመኖሩ ይጠቀሳሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም መርሃ ግብሩ የምግብ ዋስትናን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትንና የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን፣ የሕዝብን አብሮነትና ወንድማማችነት በማጠናከር እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትን በማጎልበት ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን አለም አቀፍ ገፅታና ተጽዕኖ ፈጣሪነት በማጠናከሩ ሀገሪቱ የCOP32 አስተናጋጅ እንድትሆን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በማንሳት፣ የችግኝ ተከላን ከብዛት ወደ ጥራት ማሸጋገር፣ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ መንከባከብና ለታለመላቸው የኢኮኖሚና የአካባቢ ልማት ዓላማዎች በብቃት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞች የመትከል መርሃ ግብር በመላው ኢትዮጵያ በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ እየተካሄደ ነው።

#prosperity

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party