የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ መልዕክት
በዛሬው እለት በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና በባህር ዳር ከተማ ''አርቆ ማየት አልቆ መስራት'' በሚል መሪ ቃል በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ ለክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተዘጋጀው መድረክ ላይ በመገኘት ማጠቃለያ ሰጥቻለው።
በመድረኩ የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች እቅድ የ2018 አፈፃፀም ግምገማ የተካሄደ ሲሆን በበጀት አመቱ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ አፈፃፀሞች መመዝገባቸው ተረጋግጧል። በተጨማሪም የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ኦረንቴሽን የተሰጠ ሲሆን በያዝነው በጀት አመት የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ፣ ሰላምን ለማረጋገጥ እና መልካም አስተዳደር ለማስፈን በቀጣይነት እያረጋገጡ ለመጓዝ መሰራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች ምክክር አድርገናል።
በክልሉ የወደፊት ጉዞ እና ሕዝባዊ አገልግሎት ዙሪያ ጠንካራ እና ፍሬያማ ሀሳቦች ተንፀባርቀዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለመንግስት እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለው ጠንካራ እምነት እና በሁሉም ዘርፎች የተያዙ ውጤኖች እንዲሳኩ የሚያደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና የሚቸረው ሲሆን የሕዝብ እና የሀገር አለኝታ የሆኑ ተቋማትን የሚያፈርስ «ተቋም ገዳይ» የፖለቲካ አካሄድ በጥብቅ ተወግዟል።
የአሻራ ፖለቲካ በማጎልበት፣የአመራር ጥበብ ተላብሶ ታሪክ ለመስራት ሁሉንም አቅሞች አሟጦ መጠቀም ቀጣይ የጋራ የቤት ስራችንም ይሆናል።
እህት ወንድሞቻችን መስዋእት የከፈሉበት፣ የፓርቲ አደራ፣ የህዝብ አደራና የሰማእታት አደራ ፣ አስጠብቀን ክልሉን ወደ ብልፅግና ማሻገር፣ የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላትን አቅም አሟጦ በመጠቀም ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መገስገስ ከሁላችንም የሚጠበቅ ውጤት ነው።