እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ -አቶ ተመስገን ጥሩነህ
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የመስቀል በዓል መስቀሉ ለ300 ዓመታት ከተደበቀበት የወጣበት በዓል ነው ብለዋል፡፡
መልካም የምሥራች የተነገረበትና ብርሃን የተገለጠበት በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአንድ ዘመን የተሳሳቱ ሰዎች የፈጠሩትን ጥፋት፤ በሌላ ዘመን የተነሡ ተቆርቋሪ ሰዎች አስተካክለውታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ልክ እኛ የባሕር በርን ለማስተካከል እንደምንሠራው መሆኑን አስረድተዋል ።
አስቸጋሪ የክረምት ወር አልፎ የመጸው ወር በሚብትበት ጊዜ የሚከበረው መስቀል የመደመርን ኃይል የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በአንድ በኩል ችቦዎች ተደምረው ደመራውን ይገነባሉ ያሉት አቶ ተመስገን በሌላ በኩል ደግሞ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሁሉ በተመሳሳይ ቀን፣ በተመሳሳይ አከባበር፤ እንደየብሔረሰቡ ባህል ተደምረው በዓሉን ያከብራሉ ብለዋል፡፡
“የጎመን ምንቸት ውጣ፣ የገንፎ ምንቸት ግባ” እንደሚባለው ሁሉ፣2019 ዓመት፣ አስቀድሞ መውጣት የጀመረው የኢትዮጵያ የችግርና የፈተና ምንቸት ተጠቃልሎ የሚወጣበትና የብልጽግና ምንቸት በየቤታችን የሚገባበት ዓመት እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል።