Prosperity Party

እንደ አዲስ የተሰጠን ህዝባዊ አደራ እና ቀጣዮቹ የትኩረት አጀንዳዎች

ሳምንታዊ መልዕክት 

በቅርቡ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ለብልፅግና ፓርቲ በድጋሚ የሰጠው ድምፅ፣ ሀገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የያዝነውን ራዕይ ከዳር ለማድረስ የተሰጠ ታሪካዊ አደራ ነው። እንደ ፓርቲ፤ በምርጫዉ የተገኘዉ ዘርፈ ብዙ ድል የምንዘናጋበት ሳይሆን የዜጎቻችንን የዕለት ተዕለት ህይወታቸዉ እንዲቀየርና የተሸለ ኑሮ የመኖር እንዲሁም የመልማት ፍላጎቶች እዉን ለማድረግ ለሚያስቸሉ ስራዎች ቅድሚያ በመስጠት በትጋት እንድንሰራ የተሰጠንን ኃላፊነት የምናስታዉስበት ነው።

በመጪዉ መስከረም ወር የሚጀምረው የአዲሱ መንግሥት የሥራ ዘመን፣ የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉና ሀገራዊ እድገትን የሚያፋጥኑ አበይት ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ርብርብ የሚደረግባቸዉ ስራዎች ይሆናሉ። የምግብ ሉአላዊነትንና የግብርና ዘመናዊነትን በኩታ-ገጠም እርሻዎችና በቴክኖሎጂ አቅርቦት ማረጋገጥ፣ የታዳሽ ኃይልና የኢነርጂ አቅማችንን በማሳደግ የኢንዱስትሪ መደላድላችንን ማጠናከር፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ጋዝ እና የኒዩክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አገራዊ አቅምን ማጎልበት የትኩረት ማዕከል ናቸው። በተጨማሪም፤ በአዲስ አበባ የተገኘውን አበረታች የከተማ መሰረተ-ልማትና የኮሪደር ስራዎች ተሞክሮ ወደ ሁሉም የክልል ከተሞች በማስፋት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት በመጠቀም ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን የሚቀንስ እንዲሁም የተቀላጠፈ የህዝብ አገልግሎት ማቅረብ፣ ስኬታማ በነበረዉ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በመታገዝ ዘላቂና የተረጋጋ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብርን እውን ማድረግ የሚሉትም ዋነኛ አጀንዳዎች ተደርገዉ የተያዙ ናቸው።

አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር በመጪው መስከረም ወር ተመስርቶ ወደ ስራ ሲገባም እነዚሁ አጀንዳዎች የቀን ተቀን የትኩረት አቅጣጫዎች በመሆን ይተገበራሉ። ይህ ምዕራፍ፤ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደዉ የፓርቲያችን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ በወጣዉ የአቋም መግለጫ በ3ኛነት ከሰፈረዉ “አገራዊ አቅማችንን በማጎልበት፣ አዳዲስ ዘርፎችን በመፍጠር እና የፈጠራ ኢኮኖሚን በመገንባት የኢኮኖሚ ብልፅግና ግቦቻችንን ማሳካት” ከሚለው ነጥብ ጋር በቀጥታ የሚሰናሰን ነው። በጉባኤው የተያዘው አገራዊ አቅምን የማጎልበት ውሳኔ፣ በእነዚህ አበይት አጀንዳዎች ትግበራ አማካኝነት የዜጎችን ህይወት በተጨባጭ መለወጥ ወደምንችልበት ምዕራፍ እናሸጋግረዋለን፡፡
የዚህ ጉዞ መነሻም ሆነ መድረሻ የመደመር አገራዊ ዕሳቤ ሲሆን፤ የተያዙትን አጀንዳዎች መሬት ለማውረድ ደግሞ የመላዉ ኢትዮጵያዊያንን በሀብት ፈጠራ ላይ መትጋት እንዲሁም ፖለቲካዊ ብስለትን በማዳበር የራስን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችል ጽናት እና ቁርጠኝነት መላበስ መቻል እጅግ አስፈላጊ ነው።

አሁን ባለንበት ወቅት አበይት ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እንዲሁም ኃያላን ሀገራት፣ የብልፅግና ፓርቲን ተቋማዊ ጥንካሬ፣ የአመራር ብስለትና ራዕይ፣ እንዲሁም የፖሊሲዎቻችንን ትክክለኛነት በግልጽ ተረድተዉ እውቅና እየሰጡ ይገኛሉ። የጀመርናቸው ሁለንተናዊ የልማት እና የዲፕሎማሲ ስራዎች ፍሬ ማፍራታቸው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል።
የቀጣይ ጉዟችን መዳረሻ የሚሆነዉም 2023 ዓ.ም ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያን "አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት" ማድረግ ነው። በ7ኛዉ ሃገራዊ ምርጫ ለህዝብ የገባናቸዉን ቃልኪዳኖች ሰንቆ መስከረም 2019 ዓ.ም የሚመሰረተዉ አዲሱ የመንግስት አስተዳደር፤ ይህን ግዙፍ ራዕይ ለማሳካት ይቻል ዘንድ በተሰጠው ህዝባዊ ይሁንታ እና በመደመር እሳቤ አጋዥነት የዜጎችን ህይወት ወደሚያሻሽልበት አዲስ የትግበራ ምዕራፍ ይገባል። ፓርቲያችን ብልፅግና፤ እንደ ሁልጊዜዉም የህዝብን አስተያየቶች እያዳመጠ፣ እንቅፋቶችን በድል እየተሸገረ፣ ችግሮችን እየፈታ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እና ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ያደርጋል!

ብልፅግና ፓርቲ

ነሐሴ 25፤ 2018 ዓ/ም
አዲስ አበባ

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party