Prosperity Party

ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የተጋመደ የጋራ ማንነታችን እና ትስስራችን ማሳያ ናቸው፤ እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ሳምንታዊ መልዕክት

ሀገራችን ኢትዮጵያ የአያሌ ህብረ-ብሔራዊ ባህሎችና ማንነቶች መገኛ ነች፡፡ ይህ ቀለመ-ብዙ ሀብት ከሀገራችን ምድረ-ቀደምትነት የሚመነጭ ሲሆን በጊዜ ዥረት እየዳበረ የቆየ ልዩ ማህበረሰባዊ ኩነት ነው፡፡ ይህ ኩነት በህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ሲገለጽ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት መሠረት የጸና እንዲሆን ከማስቻል በተጨማሪ የታሪክና የባህል ቀጣይነት በማረጋገጥ ባህላዊ ትስስሩ ያጠናከረ ህዝብ እና የተረጋጋ ሀገረ-መንግሥት ለመፍጠር በብዙ ሲያግዝ ቆይቷል፡፡

የሀገራችን የእምነት ትውፊቶች ይህንን የህዝቦች ትስስር እና ሀገረ-መንግሥት ፅናት በመደገፍ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በሁሉም እምነቶች የሚከበሩ በዓላት ሳይበረዙና ሳይቆራረጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ድምቀታቸው እየጨመረ በትውልድ ቅብብሎሽ እየተከበሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በዩኔስኮ የዓለም ባህል መዝገብ ጭምር በማይዳሰሱ እና በአደባባይ ቅርስነት መመዝገብ የቻሉ በዓላት በየዓመቱ አያሌ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ቀልብ ሲስቡ ይስተዋላል፡፡

ከነዚህ ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት መካከል በዛሬው ዕለት በመላ የሀገራችን ክፍል የሚከበረው የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል የሰው ልጅ ከሀጥያቱ እንዲነጻ እና ድህነት እንዲያገኝ የተከናወነ የፈጣሪ ምሳሌያዊና መሎኮታዊ ኩነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥምቀት በፈጣሪና በሰው እንዲሁም በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ አስተምህሮ ነው፡፡ ዉሀ በተፈጥሮ ከምናገኛቸው ልዩ ስጦታዎች አንዱ ነው፡፡ ካለ ዉሀ ህይወትም ተፈጥሮም የሚታሰቡ     አይደሉም፡፡ ስለሆነም ጥምቀት የፈጣሪ፣ የሰው እና የተፈጥሮ ግንኙነትና መስተጋብር የሚንጸባረቅበት ድንቅ ሀይማኖታዊ ክንዉን ያደርገዋል፡፡

ብልፅግና ሀገር በቀል ፓርቲ ሆኖ ሲመሰረት እነዚህን ህዝባዊና ሀይማኖታዊ አስተምህሮቶችና ትዉፊቶችን ታሳቢ አድርጎ ነው፡፡ ፓርቲያችን በራሱ ፖለቲካዊ አስተምህሮ መሠረት ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት በተሻለ መንገድ በመበየን የታሪክ እጥፋት መፍጠር የቻለ ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲያችን በሰው-ተኮር ፕሮግራሙ የአያሌ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ ሲያሻሽል ከተፈጥሮ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማረቅ ደግሞ የአረንዴ አሻራ ንቅናቄ በመተግበር እስካሁን 48 ቢልየን ችግኞች በመትከል የተፈጥሮ ሀብት የማዳን ታሪካዊ ሥራ ሰርቷል፡፡ ለዚህም የተለያዩ እውቅናና አድናቆት የተሰጠው ሲሆን በቅርቡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ የሆነውን COP-34 እንድታዘጋጅ መመረጥዋን የዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቻችን በዓለም መዝገብ ማስፈር እንደቻልነው ሁሉ ዓለም በብልፅግና ፓርቲ መሪነት የሚከነወኑ ሰው-ተኮርና የተፈጥሮ እንክብካቤ ሥራዎቻችን እውቅና ክብር እየሰጠን ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ በዓለምአቀፍ ደረጃ ያለንን ተሰሚነት ከመገንባት ባሻገር የጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ማሳያ የሆነውን የታሪክና የባህል ቀጣይነት ማረጋገጥ የቻልን መሆናችንን አስመስክሯል፡፡ ይህም እንደቀደሙ ሁሉ የተጋመደ ማንነታችና ትስስራችን ውጤት በመሆኑ ሁላችንም ልንኮራበትና ልንጠብቀው የሚገባ የጋራ ድላችን ነው፡፡

በድጋሜ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንልን!

ብልፅግና ፓርቲ

ጥር 11፤ 2018 ዓ/ም

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party