Prosperity Party

ዘፍርስዋ ዓዲ ይፈኻኸሩላ፤ ዘልምዕዋ ዓዲ ይመኻኸሩላ! (የሚፎካከሩባት ሀገር ትፈርሳለች፣ የሚመካከሩባት ሀገር ትለማለች)

የአንድ ሀገር ስብራቶች እና ለአለመግባባት መነሻ የሚሆኑ ተግዳሮቶች ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ችግሮችም ሊመነጩ ይችላሉ። በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ እና የፖለቲካ ገበያ ውስጥ ጎልተዉ ከሚታዩና አለመግባባትን ከሚያሰፉ ችግሮች መካከል፣ ብዘሃነትን እንደ ድልድይ ሳይሆን እንደ ግንብ የመጠቀም አባዜ አንዱ ሲሆን ለሌሎች ቦታ ባለመስጠት እኔ ብቻ ልደመጥ ማለት ወንድምን እንደ ባላጋራ፣ ብዝሃነትን እንደ አደጋ እንዲቆጠር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ቀደምት አባቶቻችን ዘፍርስዋ ዓዲ ይፈኻኸሩላ ዘልምዕዋ ይመኻኸሩላ (የሚፎካከሩባት ሀገር ትፈርሳለች፣ የሚመካከሩባት ሀገር ትለማለች) ሲሉ ያለ ምክንያት አልነበረም።

ፖለቲካችን እኔ ብቻ እያለ፣ በእብሪት ተሞልቶ እየተጯጯኸ የመቆየቱ ነገር እንዳለ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜያት አንስቶ የምንታዘበዉ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች ሀሳብ በሚንሸራሸርባቸዉ መድረኮች የምንታዘበዉ ችግር ደግሞ መድረኮቹ የዉይይትና የመግባቢያ መድረክ ከመሆን ይልቅ የፉከራ እና የዘለፋ አውድማ እየሆኑ የመምጣታቸዉ ጉዳይ ይጠቀሳል።

የመደመር ቀመር- ፍሪሊየን

ፖለቲካ የሃሳብ ገበያ እንጂ የጥላቻ መድረክ መሆን የለበትም። ዜጎች ከፉከራ ወጥተው ወደ መደማመጥ እና መመካከር መሻገር ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ የጩኸት እና የፉከራ አዉድ መካከል፣ የመደመር ፍልስፍና መዉጫ መንገዶቹን ያመላክታል። ብልጽግና ፓርቲ የሚመራበት ይህ ሃገር በቀል እሳቤ፤ ከተለመደ የፖለቲካ መፈክርነት በዘለለ የሀገር ግንባታ ማዕቀፍ ወደ መሆንም የተሸጋገረ እይታን የሚከተል ነዉ፡፡ መደመር፤ በልዩነት ዉስጥ ያለን ውበት የሚያጎላ፣ የተበተነን የሚሰበስብ አቅም አለዉ።

የመደመር ጉልበት

የብልጽግና ጉዞ የሚጀምረው ከፉከራ ወደ ምክክር ስንሸጋገር ነው። መመካከር ማለት እውነት በአንድ ወገን ብቻ እንደሌለች መቀበል ነው። መመካከር ማለት የኢትዮጵያ ትልቅነት ያለው በጯጯህ ሳይሆን በመደማመጥ ውስጥ መሆኑን ማመን ነው።

ይህ ንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ተተግብሮም ዉጤት የተገኘበት አካሄድ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዚህ ውጤት ነው። በፉከራ ቢሆን ኖሮ፣ ፕሮጀክቱ በወረቀት ላይ ብቻ በቀረ ነበር። ነገር ግን በመደማመጥ፣ በመመካከር እና በትብብር አሳክተነዉ የጋራ ህልማችን ማረጋገጫ ለመሆን በቅቷል። በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተገኘዉ ስኬትም ኢትዮጵያውያን ተደማምጠዉ በጋራ ያሳኩት ድል ነው።

ወሳኞቹ እኛዉ ነን

ኢትዮጵያውያን ሁለት ምርጫዎች አሉን። እየተፎካከርን፣ እየተጯጯህን እንቀጥላለን ወይስ መደማመጥና መመካከር ይሻለናል? አፍራሹን የፉከራ መንገድ ወይስ የሚያሻግረንን የምክክር ጎዳና እንመርጣለን?

ሃገራዊ ብልጽግናችን እዉን የሚሆነዉ ልዩነትን በማስጮህ ሳይሆን አንድነትነትን በማጠንከር ነዉ። ኢትዮጵያ ከተመፅዋችነት እና ጥገኝነት ወጥታ ለሌሎች የምትተርፍ ሀገር እንድትሆን፣ ራዕያችን እንዲሳካ፣ ከፉከራ ወደ ምክክር መሸጋገር የግድ ይላል። የሚመካከሩባት ሀገር ትለማለችና።

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party