በብልፅግና ፓርቲ የሶማሊ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ለ7ተኛው አገራዊ ምርጫ መወዳደሪያ የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ መርሀ-ግብር አካሄደ።
በመርሐግብሩ ላይ የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ ፣ የሶማሊ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ኢ/ር መሀመድ ሻሌ ፣ የተለያዩ የክልሉ መንግስትና የፓርቲው አመራሮች እንዲሁም በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሁመድ የብልፅግና ፓርቲ ምልአተ ህዝቡን በንቃት በማሳተፍና በቁርጠኝነት በመስራት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝቡ የገባውን ቃል ስኬታማ በሆነ ሁኔታ መፈፀሙን ገልፀዋል።
በክልሉ ባለፉት ስድስት አመታት በሰላምና ፀጥታ ፣ በልማት ፣ በመሰረተ ልማት እና በሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን በመተግበር ለህዝቡ የገባነውን ቃል በተግበር ለመፈፀም መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በቀጣይም በክልሉ የሚካሄዱ የሰላምና ሁለተናዊ የልማት ስራዎችን በእጥፍ በማሳደግ ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት ክልል ለማድረግ የጀመርነውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሶማሊ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ኢ/ር መሀመድ ሻሌ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በመርሐግብሩ ላይ የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክትን ለማስተዋዉቅ መቻሉን ገልፀዋል።
ቃልን በተግባር መፈፀም የብልፅግና ፓርቲ መግለጫ በመሆኑ ፓርቲው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለህዝቡ የገባውን ቃለ ለመፈፀም በክልሉ በተከናወኑ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል ።
በክልሉ የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊና ፍትሀዊ በሆነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ፓርቲው በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀስ ነው ሀላፊው የተናገሩት።
በመርሀ-ግብሩ ላይ የክልሉ የመንግስትና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።