2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የትጋትና የስኬት ዓመት ነበር - አቶ አደም ፋራህ
ዛሬ ሀምሌ 07/2017 ዓ.ም የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ ስራዎች ማጠቃለያ የግምገማ መድረክ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት 2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የትጋትና የስኬት አመት ነበር።
ፓርቲውን በሰብዓዊና በቁሳዊ ሀብት ማጠናከር፤ በዘመናዊ መረጃ ማደራጀት፤ ዲጂታል ብልፅግና እውን ከማድረግና ገዥ ትርክትና ቅቡልነት ከማረጋገጥ አኳያ በትጋት የተከናወኑ ስራዎች ስኬታማ ናቸው ብለዋል።
በአስተሳሰብ፤ በአደረጃጀትና በአሰራር የተዋሃደ ፓርቲ ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩ የተናገሩት አቶ አደም ፋራህ፥ በዚህም የፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ እና አምስተኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተቀናጀና በተናበበ መንገድ መሳካት ችሏል ነው ያሉት።
የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው እንዲሆን በትኩረት ተሰርቷል በዚህም አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ህዝቡን በማሳተፍ በተቀናጀ መንገድ መስራት በመቻሉ በአገራችን አንፃራዊ ሰላም መስፈን እንደቻለ ተናግረዋል።
በንቅናቄ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ያወሱት ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ፥ ከተረጂነት ለመውጣት የተከናወኑ ስራዎች የሀገራችንን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር መሰረት የጣሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው እንደጠቀሱት ህዝቡ አካታችች ሀገራዊ ምክክር ላይ እንዲሳተፍ መሰራቱን አመላክተዋል፤ በዚህም አካታች ሀገራዊ ምክክር ሂደት በተሳካ መንገድ እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።
ገዥ ትርክትና ቅቡልነት እንዲረጋገጥ በመሰራቱ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ አዎንታዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ድሎችን ማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ ህዝብን በማሳተፍ መስራት ይገባል ብለዋል።