ከተማ አስተዳደሩ ለታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ሰጥቷል።
የእውቅና መርሀግብሩ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አይናለም ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሀገርን ከድህነት ለማላቀቅና ልማትን ለማረጋገጥ የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸውን በማሳደግ የማህበረሰቡን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በከተሞች እድገት፣ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ዘርፎች ለተመዘገቡት ጉልህ ስኬቶች የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚታየው ሁለንተናዊ ለውጥ ያለታማኝ ግብር ከፋዮች አስተዋጽኦ ይሳካል ተብሎ የሚታሰብ አለመሆኑን ገልጸው፥ አዲስ አበባ ከተማ እንደገና እንድትሰራ ማድረጋቸውንም አፈ ጉባኤው ጠቅሰዋል።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ዉድ ታማኝ ግብር ከፋዮች መዲናችን ከእናንተ በምትሰበስበዉ ገቢ በከተማችን በአስደናቂ ሁኔታ የተገበርናቸዉ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ፣ የህዝቡን የኑሮ ጫና ያቀለሉ ስራዎች ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ ከተማችንን ለቢዝነስ እና ለመኖር የተመቸች ንፁህ ፣ ጤናማ አካባቢ እና በአለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭና ተወዳዳሪ እየሆነች ይገኛል ፤ ይህ ለዉጥ በርግጥ ለእናንተም ተጨማሪ አሴት፣ለቢዝነስ ማህበረሰቡ ተጨማሪ የሀብት መፍጠሪያ ምንጭ ነዉ ብለዋል።
ከንቲባዋ አክለውም በቀጣይ በግብር አሰባሰብ ዙሪያ የአገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ፣ በማዘመን እና ተጠያቂነትን በማስፈን ክፍተቶችን እየሞላን ፣ እፀፆችን እያረምን የሁለንተናዊ ብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ከተማን እንገነባለን ሲሉ አንስተዋል።