የብልፅግና አዲሱ መንገድ፡ የመደመር ርዕዮት
ኢትዮጵያ፥ የፖለቲካ ጉዟችን ረጅም ታሪክ ውስጥ የሌሎችን ሀገራት ርዕዮተ ዓለም በመቅዳትና ያንኑ ገቢራዊ ለማድረግ ብዙ ጊዜዋን አሳልፋለች። ከሌሎች ሀገራት የተቀዳውን ርዕዮት ለማስከበር ስንል ያገኘነው ውጤት ድህነት፣ ቂምና ቁርሾ፣ መፈራረስ፣ መካረር፣ ጽንፈኝነት እና ውድ የሕይወት መስዋዕትነት መክፈል ሆኗል።
የቀደመዉ የፖለቲካ መንገዳችን ችግራችንን ትንትኖ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ፤ በሌላ አዉድ ዉስጥ ለሌላ ችግር ተብለው የተቀመጡ ርዕዮተ ዓለሞችን በግድ ለመተግበር ሞክረናል። በዚህም ምክንያት "አብዮት ልጆቿን ትበላለች" ወይም "በመቃብሬ ላይ" የሚሉ አክራሪ አመለካከቶች የፖለቲካ ባህላችን አካል ሆነው ክፍፍልን አጠንክረዋል። ውጤቱም በርካታ ዜጎቻችን በእርስ በርስ ግጭቶች ሕይወታቸውን አስከትሏል፡፡ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችንም ቀጣይነት እንዲኖረዉ እድል በመስጠት እንደ ሀገር ከድህነት አረንቋ እንዳንወጣ በማድረግ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
በዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከጠባብ ርዕዮተ ዓለም ወደ ሕዝብ ማዕከላዊነት ያሸጋገረ ያልተኬደበት አዲስ መንገድ ይዞ ቀርቧል፡፡ ይህ አዲስ የብልፅግና የፖለቲካ መንገድ የመደመር ርዕዮት ይባላል፡፡
ብልፅግና ርዕዮተ ዓለምን በሚመለከት ያለው አቋም ከቀድሞ የፖለቲካ ባህላችን ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህ አዲሱ አቀራረብ ለየትኛዉም የሀገር ዉስጥ ችግር መፍትሄ ከውጭ መቅዳት ሳይሆን ከራሳችን ችግር ትንተና መፍትሄ መስጠትን ምርጫዉ ያደርጋል፡፡
በቀድሞ ታሪካችን፣ ተመሳሳይ ርዕዮት ያላቸው ፓርቲዎች እርስ በርስ እንደ ጠላት ይፈራረጁ ነበር። ምክንያቱም ችግራችንን ለመፍታት ከመሞከራችን በፊት፣ በውጭ ሀገር ፍላጎት ልክ ተቀዶ ለተሰራ ርዕዮት ታማኝ ለመሆን እንጥር ስለነበርን ነዉ። አዲሱ የመደመር ርዕዮት ግን የትኛዉንም ችግር ከኢትዮጵያ ተጨባጭ እዉነታ አኳያ በመተንተን መፍትሄ መስጠትን ያበረታታል።
ከዚህ ቀደም ርዕዮተ ዓለም ኢትዮጵያን ከአንድ ጎራ ጋር ብቻ እንድትተሳሰር አድርጓታል። አዲሱ መንገድ ግን ከየትኛውም የዓለም ክፍል ጋር ለመተባበር፣ ሀብት ለማሰባሰብ እንቅፋት አይሆንም። ታማኝነቱ ለጠባብ ርዕዮት ሳይሆን ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ግብ ነው።
በርዕዮተ ዓለም ስም ሰው መግደል "አብዮት ልጇን ትበላለች" ተብሎ ሲወደስ ኖሯል። አዲሱ መንገድ ግን ርዕዮትን እንደ መጨረሻ ግብ አይቆጥረውም። የርዕዮት ጥንካሬ የሚመጣው ለሕዝብ ብልጽግና ባለው ፋይዳ፣ አዋጭነትና አግባብነት ነው። የዓለም እውነታ እንደሚያሳየን፣ ሶሻሊዝም ያሉ ሀገራት ከሊበራሊዝም፣ ሊበራሊዝም ያሉ ሀገራት ከሶሻሊዝም እየተማሩ "ገቢር ነበብነት" (Pragmatism) እየተገበሩ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ አቋም ግልጽ ነው፦ ርዕዮተ ዓለም ራሱ መዳረሻ አይደለም፤ መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋጥ ነዉ፡፡
የምንገሰግስበት መንገድ ደግሞ፦ ዴሞክራሲያዊ እና ሁሉን አቀፍ ተሳታፊነትን መሰረት ያደረገ፣ በአብዛኛው በዛሬና ነገ ላይ ያተኩር፣ ትላንትን ለትምህርት ብቻ የሚጠቀም፣ ከሁሉም ጠቃሚ ነገር ጋር ለመደመር ዝግጁ የሆነ አቀራረብ ነው።
ይህ የመደመር ርዕዮት ከሁለት ጫፍ አክራሪነት የጸዳ፣ ገቢር ነበብነትን የሚያጎላ እና የኢትዮጵያን ልዩነቶች ከማጥፋት ይልቅ ለሀገራዊ ብልጽግና ማቀናጀትን የሚያስችል አዲስ ጅማሬ ነው። ባለፉት የለዉጡ ዓመታት ፓርቲያችን በወሰደዉ ቁርጠኝነት አዲስ የመደመር ርዕዮት የኢትዮያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ የምትፈልገው መለያየትን፣ መፈራረስን ሳይሆን መደመርን፣ ጠባብ አላማን ሳይሆን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ነው። ይህ አዲሱ መንገድ የወደፊት ትውልድ በኩራት የሚዘክረው የጋራ ጉዞ በመሆኑ ሁላችንም ለዚህ አላማ ስኬት በቁርጠኝነት መስራት ይገባናል፡፡