ምርጫ እና ምክክር የዘላቂ ሰላም፣ ህብረብሔራዊ አንድነት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕያችን የምናሳካበት መንትያ መንገዶች ናቸው- ሳምንታዊ መልዕክት
ከሁሉም ቀድማ በዓለም ሥልጣኔ የመገለጥ ከፍታ የነበራት ሀገራችን ኢትዮጵያ በድህነትና ኋላቀርነት ስሟ መነሳቱ ሊያበቃ ይገባል የሚል ቁጭት የሰነቀዉን የለውጥ መንግሥት እስካሁን አያሌ የሪፎርም ሥራዎች በመሥራት ዝላይ እና ተስተካካይነት የፈጠሩ ሰፋፊ ውጤቶች አስመዝግቧል፡፡
ከነዚህ ሪፎርሞች መካከል ለዘመናት አብሮን የዘለቀና ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍለን የቆየው የዴሞክራሲ ባህል ስብራታችንን ትርጉም ባለው መልኩ ለመጠገን የተሰራው ሥራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በህገ-መንግሥቱ መሠረት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንዲተገበር ከማድረግ እስከ የዴሞክራሲ ባህላችን መገንባት እና ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ የዘለቁ ብስለት፣ ቁርጠኝነትና አሳታፊነት የሚጠይቁ አያሌ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
የዴሞክራሲ ባህላችን ላይ የሚታየውን ስብራት ለመጠገን የመግባባት-ዴሞክራሲ እንደ ሁነኛ መፍትሄ እየተተገበረ ሲሆን የዚሀ ጥረት ማዕከል የሆነው ደግሞ የሀገራዊ ምክክሩ ሥራ ነው፡፡ የዛሬ ስድስት ዓመት ገለልተኛ ኮሚሽን ሆኖ በመዋቀር ወደ ሥራ የገባውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎች የመሰብሰብ ሥራውን ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ማሸጋገር ችሏል፡፡
ወደኋላ ቀርቶ የቆየውን የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ በክልሉ ለማከናወን የተደረጉ በርካታ ጥረቶች እዛ ባለው ጎታች ኃይል ምክንያት አለመሳካቱ ተከትሎ የክልሉ ተወላጆች በብዛት በሚኖሩባት እና የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ቤት በሆነችው አዲስ አበባ ለሦስት ቀናት አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ መድረኩ ከትግራይ ክልል ለዚሁ ሲባል የመጡ ተሳታፊዎች ያካተተ ከ600 በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሲሆን ሂደቱ እጅግ የላቀ የመግባባትና የለውጥ መሻት የታየበት፣ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት በምሉዕነት የሚያንጸባርቁ አጀንዳዎች ነጥረው የወጡበት፣ በላቀ የተሳታፊዎች ብስለትና ዲሲፕሊን ታጅቦ እና በነጻነትና በዴሞክራሲያነት ተሞልቶ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ብልፅግና ፓርቲ ጨምሮ 12 ክልሉ ማዕከል ያደረጉ ክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ስፋትና ጥልቀት ያለው ምክክር አካሄደው 11 ዋናዋና አጀንዳዎችና 51 ዝርዝር አጀንዳዎች ምክክር እንዲደረግባቸውና መፍትሄ እንዲፈለግላቸው በማለት ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
ይህ ሥራ እንደ ሀገር መፍጠር ለምንሻቸው የመግባባት፣ የዕርቅ እና የዘላቂ ሰላም ዓላማዎች መሳካት አይነተኛ ሚና አለው፡፡ ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አጀንዳዎች ከሞላ ጎደል የሚመሳሰሉና የሚቀራረቡ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ መድረኩ በአዲስ አበባ መካሄዱም የትግራይ ህዝብ እኔ ብቻ አውቅልሀለው ከሚለው የማያግባባና ኋላቀር አስተሳሰብ የመላቀቅ ሂደት ላይ ተስፋ የፈነጠቀ ሆኖ ታይቷል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎችም አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እንዲጀመር ያላቸዉን ከፍተኛ ፍላጎት ባሳየ መልኩ በሙሉ ፍላጎት ሲሳተፉና ሲተባበሩ ተስተዉለዋል፡፡
ባጠቃላይ የሰሙኑ የትግራይ ክልል የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ የምክክር ኮሚሽኑ የዓመታት ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የደረሰበት፣ ሁሉም አጀንዳዎች በአሳታፊነት፣ እኩልነት እና ፍትሀዊነት መሰብሰብ የተቻለበት እንዲሁም መጻኢው ጊዜ አዎንታዊ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባት እና ሁለንተናዊ ልማት የሚነግስበት መሆኑ ያለንን ተስፋችን ከፍ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተስተዉሏል፡፡
ይህም እየተሳካ ከሚገኘው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በመንትያነት ተደምሮ ሲታይ እንደ ሀገር ምን ያክል ትልቅ ተስፋ እንዳለን በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ትመርጣለች፤ ትመክራለችም፤
በምርጫና በምክክር የሀገረ-መንግሥት ግንባታዋ ወደ ላቀ ደረጃ ታደርሳለች፤
ብልፅግና ፓርቲ
መጋቢት 28፤ 2018 ዓ/ም