Prosperity Party

የመደመር ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ እያሸጋገረ ይገኛል!

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ እያሳየች ያለው ማንሠራራት በተለዋዋጭ የዓለም አሰላለፍ ውስጥ ያሉ ዕድሎችን በመለየት፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ትብብር ጋር በማስተሳሰር የውጭ ግንኙነቷን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረች ነው። የብሪክስ አባልነትም የዚህ የዲፕሎማሲ ማንሠራራት ጉልህ ማሳያ ነው። ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ አሁን 11 ሙሉ አባላት ያሉት ሲሆን በሩሲያ ካዛን ጉባኤ ይፋ የተደረጉ 10 አጋር ሀገራትንም በልዩ የአጋርነት ማዕቀፍ በማካተት ተጽዕኖውን አጠናክሯል። 

ኢትዮጵያ በ2024 የብሪክስ አባል በመሆኗ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብርን በሚያጠናክረው አለም አቀፍ መድረክ በሆነዉ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ውስጥ የራሷን ድምፅ የበለጠ አጠናክራለች። ይህ መድረክ ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ የራሷን አቋም ለማስቀመጥ፣ አጋርነቶቿን ለማስፋትና ብሔራዊ ጥቅሟን በተሻለ ደረጃ ለማስከበር አዲስ የዲፕሎማሲ ዕድል ከፍቷል።

በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት የዚህን አዲስ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በግልጽ ያሳያል። በብሪክስ ውስጥ ያሉት ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ገበያ በመጣመር የበለጠ ዕሴት መፍጠር እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያም በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም ከዓለም አቀፍ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ገበያ ጋር በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር ያላትን ዝግጁነት አስቀምጠዋል።

ይህ አቋም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከተለመደው የግንኙነት አድማስ በላይ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል። ዲፕሎማሲው ከፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ዕድል መፍጠር፣ ከግንኙነት ወደ አጋርነት፣ ከአጋርነት ወደ የጋራ እሴት መፍጠር እየተሸጋገረ ነው።

የብሪክስ ለኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ከማስፋት ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታንና የአፍሪካን የልማት አጀንዳ የማስቀጠል እድልም ይፈጥራል። በዚህ መድረክ ኢትዮጵያ የምትፈልገው የሌሎችን ሀብት መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ የራሷን ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ የምርት አቅምና ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ወደ ዓለም አቀፍ የጋራ እሴት መፍጠሪያ ማዕከል መቀየር ነው።

በኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት/WTO አባልነት ጥያቄ ላይ ከብሪክስ አባል ሀገራት ያገኘችው ድጋፍም የዚህ የተሳትፎ ዲፕሎማሲ ተጨባጭ ፋይዳ ነው። የሀገራችን ድምፅ በተለያዩ የዓለም መድረኮች እየተሰማ መምጣቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አጀንዳ ቀረፃ ውስጥ ያላትን ሚና እያጠናከረ መሆኑን ያረጋግጣል። 

የመደመር መንግስት የሚከተለዉ  ዲፕሎማሲ ዓለምን በወዳጅና በጠላት የሚከፋፍል ሳይሆን፣ በጋራ ጥቅም የሚያስተሳስር ዲፕሎማሲ ነው። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከአፍሪካ ጥቅም፣ የአፍሪካን ጥቅም ከደቡብ- ደቡብ ትብብር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሂደት ውስጥ የራሷን ቦታ የምታጠናክርበት መንገድ ነው። በአሁን ጊዜ ኢትዮጵያ ከተመልካች ወደ ተዋናይ፣ ከተጠቃሚ ወደ አምራች፣ ከተሳታፊ ወደ አጀንዳ ቀራጭነት ሚና እየተሸጋገረች ነው። ይህም የዲፕሎማሲው ማንሠራራት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላት ሚና እየተቀየረ ተሰሚነቷም እየጨመረ መምጣቱ ማሳያ ነው።

#prosperity

በብዛት የታዩ ዜናዎች

News Card List
Prosperity Party