7ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለዉ እንዲሆን ለማስቻል የወጣቶች ክንፍ አመራሮችና አባላት ተልዕኳቸዉን ሊወጡ ይገባል- አቶ አደም ፋራህ
የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት ወጣቶች ክንፍ የ2018 ዓ.ም እቅድ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እካሂዷል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ላይ ተገኝተዉ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንዳሉት፤ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አመራሮች እና አባላት 7ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለዉ እንዲሆን የማስቻል ትልቅ ተልዕኮ የተጣለባቸዉ እንደመሆኑ ሃላፊነታቸዉን በአግባቡ ተረድተዉ በላቀ አፈፃፀም ሊወጡ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
መላዉ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አደረጃጀት አመራሮችና አባላት ምርጫዉ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና አሳታፊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸዉን ሚና ከመጫወት በተጨማሪ ከሃገራችን የህዝብ ቁጥር ዉስጥ ሰፊ ድርሻ ያለዉ ወጣቱ የማህበረሰብ ክፍል የቴክኖሎጂ መተግበሪያን ጨምሮ በቀረቡት አማራጮች በመራጭነት በመመዝገብ ህገ-መንግስታዊ መብቱን እንዲጠቀም እና በድምጽ መስጫ እለትም በነቂስ ወጥቶ ድምጽ እንዲሰጥ ለማስቻል በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸዉ አስገንዝበዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ አደረጃጀት የፓርቲዉን ትልቅ ተልዕኮ ያነገበ እንዲሁም በብሄራዊነት ትርክት የታነጸ ትዉልድ በመገንባት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ታላቅ ራዕይ ያለዉ ስትራቴጂያዊ ኃይል መሆኑን ጠቅሰዉ፤ በሁሉም መስኮች ለተገኙ ስኬታማ አፈጻጸሞች የላቀ ሚና እንደተጫወተና በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮችም የተጣሉባቸዉን ቀጣይ ኃላፊነቶች ለመወጣት በበለጠ ትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸዉ አስረድተዋል፡፡
የብልፅግናን ራዕይ፣ የኢትዮጵያን ህልም፣ የመደመር እሳቤን እና የብሄራዊነትን ትርክት ማስረጽ ከወጣቶች ክንፍ አደረጃጀት የሚጠበቁ ዋና ዋና ተልዕኮዎች መሆናቸዉን በማብራሪያቸዉ በማስታወስ፤ አባላት ዘመኑን የዋጀ እዉቀት እንዲላበሱ በማስቻል፤ ተግባራዊ አፈፃፀም ላይ ግንባር-ቀደም አርዓያዎች እንዲሆኑ በማድረግ፤ እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችንም ጭምር በማነቃነቅ፣ በማብቃትና በማስተሳሰር ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ የማድረግ ሃላፊነቶች እንዳሉባቸዉ አሳስበዋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ምርጫዉ ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማንነት ያለዉ እንዲሆን እንደ ፓርቲ የያዘዉን ግብ ለማሳካት ይችል ዘንድም የወጣቶች ክንፍ በቁርጠኝነት፣ በስነ ምግባር እና በሀሳብ የበላይነት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡