"ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የዜጎችን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንሰራለን"- አቶ ብርሃኑ ፈይሳ
የብልፅግና ፓርቲ የሀብት አስተዳደር ዘርፍ በሀዋሳ ከተማ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማና የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ አጠናቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የሀብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ከዋና ጽ/ቤት እስከ ቅርንጫ ጽ/ቤቶች በበጀት አመቱ 6 ወራቶች ዉስጥ የተሳካና የተቀራረበ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል።
እንደ ፓርቲ ጠንካራ ፓርቲ፤ ጠንካራ መንግስት እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት እየተሰራ በመሆኑ ይህ እንዲሳካ በየደረጃው ያለ መዋቅራችንን ቀን ከሌሊት ጠንክሮ በመስራት ሚናዉን መወጣት አለበት ብለዋል።
የፓርቲው መመሪያ፤ ደንቦችና አሰራር ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ በማድረግ የፓርቲውን ፕሮግራም በማስፈፀም የዜጎችን የላቀ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ሀገርን የሚያሻግሩ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ከላይ እስከ ታች ያለዉ የፓርቲው መዋቅር ተልእኮውን መሸከም የሚችል በዲሲፕሊን የታነፀ፤ ብቁና ከቴክኖሎጂ ጋር የተዛመደ የሰዉ ሀይል በማብቃትና ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር የፓርቲው ህልሞች እና ራዕይ ከግብ እንዲደርሱ በትኩረት እንደሚሰራና በቀሪ 6 ወራቶች ዉስጥ የክትትል እና ድጋፍ ስርአት እስከ ቀበሌ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሌላ በኩል አቶ ብርሃኑ አፅንኦት ሰጥተዉ የተናገሩት የተጀመረው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሰምር 7ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላዉ አባላት ሀላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀት አለበት ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የግዢና ንብረት አሰተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም ሙክታር በበኩላቸው ከክልል አንስቶ እስከ ወረዳ ድረስ የብልፅግና ፓርቲ የቢሮ ግንባታ አፈፃፀሞች ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልፀዉ የፓርቲውን ሀብትና ንብረት ምዝገባና አያያዝ ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ያለፉት 6 ወራቶች የሁሉም ክልል እና ከተማ አስተዳደር ሪፖርት ቀርቦ ጥንካሬዎች እና ዉስንነቶች የተለዩ ሲሆን ስኬቶች እና ድሎችን አጠናክሮ በማስቀጠል እንዲሁም የተለዩ ክፍተቶችን የቀሪ ስድስት ወራት የእቅድ አካል አድርጎ በመፈፀም ወደ ጥንካሬ መቀየር እንሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።