የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ አመት የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ማጠቃለያ መድረክ መካሄድ ጀመረ
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፤ የየብልፅግና ፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ቡድን አባላት ተገኝተዋል።
"በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከጥቅምት 19 እስከ 30 በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደ ሀገር ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የስራ መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ስለድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አላማ ባብራሩበት ወቅት እንደገለፁት በክቡር የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በ2018 ዓመታዊ የከፍተኛ አመራር ስልጠና ማጠቃለያ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና የስራ መመሪያዎች አፈጻጸም መገምገም ነው።
አቶ አደም ፋራህ አክለው እንደገለፁት፥ በዛሬው መድረክ የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አባላት በምልከታቸው ያገኟቸውን ተሞክሮዎች የጋራ ማድረግና በቀጣይነት በፌዴራል መንግሥት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለመየት ነው።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን አባላት በሁሉም ክልሎችና ሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ባለፋት ስድስት ወራት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኑሮ ውድነት ለመቀነስ፣ ከተረጅነት ለመውጣት፣ የኮሪደር ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና ሌሎች የልማትና መልካም አስተዳደርና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን አፈጻጸም አቅርበው ግምገማ ይደረግባቸዋል።