የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የሀገር ህልውና ምሰሶዎች ናቸው- ሳምንታዊ መልዕክት
እንኳን ለኢትዮጵያ አየር ሀይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓል አደረሰን!
ኢትዮጵያ ሀገራችን በሩቅና በቅርብ ጠላቶች የማትደፈር እንድትሆን ካስቻሏት ተቋማት የጸጥታ ደህንነት ተቋማት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሀገራዊ ተቋማት ዘመኑን የዋጁ እና በፍጥነት በሚለዋወጠዉን የዓለም የሀይል ሚዛን ብቁ መደላድል እንዲፈጥሩ በማስቻል የሀገር ህልውና፣ ደህንነትና ክብር እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡
ይህ ለአፍታም የማይዘነጋ ቁልፍ ሀገራዊ ተልዕኮ በምልዓትና በአስተማማኝነት ለማሳካት ተቋማቱን በሰው ሀይል፣ በሎጂስቲክስ፣ በቴክኖሎጂና በህዝባዊነት እንዲጠናከሩ ተደርገዋል፡፡ በሀገራዊ ለውጡ ትኩረት ተሰጥቷቸው በተከታታይነት ከተገነቡ ተቋማት አንዱና ዋነኛ እነዚህ የሀገር ህልውና ምሰሶ የሆኑት ተቋማት እንዲሆኑ የተደረገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ከነዚህ ተቋማት አንዱ በመሆን ለኢትዮጵያ የሚመጥን አያሌ ሪፎርም ሲያካሄድ እና በተግባር የሀገር ሉአላዊነት ሲያስከብር ቆይቷል፡፡ ይህ በሪፎርምና በተግባር ተፈትኖ የተጠናከረው የአየር ሀይላችን በተቋማዊ ገለልተኝነት መርህ የህዝቦች የዘመናት መሻት የሆነዉን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ራዕይ አካል በመሆን ሀገራዊ ለውጡን በአስተማማኝ ጎዳና ወደ ፊት እንዲገሰግስ አልኝታነቱን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሀይል 90ኛ ዓመት ሲከበር የተቋሙን አንጋፋነት፣ አሁን የደረሰበት የላቀ ደረጃ እና ቀጣይ ግስጋሴ በማጣመር ነው፡፡ ይህም ዜጎች በሀገራቸው ተቋማዊ አቅም እንዲተማመኑና እንዲኮሩ ከማስቻል በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለመድፈር የሚቃጡ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች ሴራዎች የማይሳኩ ከንቱ ምኞቶች መሆናቸውን ተገቢውን መልዕክት አስተላልፏል፡፡ “ሰማዩ የኛ ነው” የሚለው የተቋሙ መፈክርም እየተኖረ ያለ ሀገራዊ ራዕይ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ከሀገራችን የለውጥ መሻት አንጻር የነዚህ ተቋማር ሪፎርም ገና ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ከአጠቃላይ ሀገራዊ የልማትና የብልፅግና ራዕይ ጋር እየተሰናሰነ ይሄዳል፡፡ ይህ መሰናሰንም ከሀገር ግንባታ አንጻር አይነተኛ ሚና እንዲጫወት ይደረጋል፡፡ ይህ አቅም ሀገራችንን ከወረራና ከግጭት አዙሪት እንድትላቀቅና ጦርነትን ከሩቁ ለማስቀረት እንድትችል ከማድረግ ባሻገር የኢትዮጵያ ብልፅግና አያቀሬነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
መልካም የኢትዮጵያ አየር ሀይል 90ኛ ዓመት ምስረታ በዓል!
ብልፅግና ፓርቲ
ጥር 18፤ 2018 ዓ/ም