የዲፕሎማሲያችን አዲስ ምዕራፍና የብልጽግና ጉዟችን!
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያስመዘገበችው ጉልህ የዲፕሎማሲ ትርፍና የውጭ ግንኙነት ስኬት፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስርና ለጋራ ተጠቃሚነት አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ ሆኗል። ብልጽግና ፓርቲ ሀገርን የመምራት ሃላፊነቱን ከተረከበ ወዲህ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በልመናና በጥገኝነት ላይ ሳይሆን በክብር፣ በብሄራዊ ጥቅም እና በጋራ እድገት ላይ እንዲመሰረት አድርጓል።
በመሆኑም ከስጋት ፖለቲካ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የተሸጋገርንባቸውን አራት የድል ምሶሶዎች እነሆ፦
1. የቀጣናዊ ትስስርና የጎረቤት ሀገራት ወዳጅነት
ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም ሳታከብር የራሷን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደማትችል አጥብቀን እናምናለን። መደመር ለቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትም የሚተርፍ እሳቤ በመሆኑ፣ በምስራቅ አፍሪካ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ትስስር ስራዎቻችን የዚሁ ውጤቶች ናቸው። ከጅቡቲ፣ ከኬንያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ወ.ዘ.ተ ጋር ያለን የንግድና የመሰረተ ልማት ትስስር ለአፍሪካ ቀንድ ብልጽግና መሰረት እየጣለ ይገኛል።
2. የብሪክስ+ (BRICS+) አባልነትና የዓለም አቀፍ ሚዛን መሪነታችን
ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የዓለምን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሚዛን እየቀየሩ ካሉ ሀገራት ጋር (BRICS+) በጋራ ለመስራት መመረጧ፣ የፓርቲያችን የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ምን ያህል የበሰለና ጊዜውን የዋጀ መሆኑን ያሳያል። ይህ አጋርነት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠንና የሀገራችን ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልቶ እንዲሰማ ለማድረግ ትልቅ አቅም ፈጥሮልናል። ኢትዮጵያ ዛሬ ተከታይ አይደለችም፤ በዓለም አቀፍ አደባባይ አጀንዳ ቀራጭ እንጂ!
3. ታላቁ የህዳሴ ግድብና የሉዓላዊነት ድል
በዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችና ፈተናዎች ውስጥ ሆነን፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ሳናስደፍር ግድባችንን ለዚህ ደረጃ ማብቃታችን የብልጽግና ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ነው። "ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካዊ መፍትሄ" የሚለውን መርህ በተግባር በማሳየት፣ በአፍሪካ ህብረት ስር የተካሄዱ ድርድሮች የሀገራችንን የዲፕሎማሲ የበላይነት ያስመሰከሩ ነበሩ። አባይ ዛሬ የልማታችን ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማሲያዊ ጽናታችን ምልክት ነው።
4. የዲያስፖራው ተሳትፎና ህዝባዊ ዲፕሎማሲ
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና ድጋፍ ወደ ተደራጀ አቅም እንዲቀየር ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። በታላቁ የኢትዮጵያ ጥሪና በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች የታየው የዲያስፖራው ተሳትፎ፣ ሀገራችን በውጭ ጫናዎች እንዳትበረከክ ታላቅ ግንብ ሆኖ አገልግሏል። ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያችን ኢትዮጵያዊነትን በዓለም አደባባይ በክብር እንዲቆም አድርጎታል።
በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ስኬት ሚስጥሩ " የሀገር ክብርን ማዕከል ያደረገ ዲፕሎማሲ" ነው። ወደፊትም ቢሆን የሀገራችንን ሉዓላዊነት በመጠበቅ፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ከወዳጅ ሀገራት ጋር ያለንን ትብብር በማጠናከር፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ስራችንን እንቀጥላለን።
ለእውነተኛ ሉዓላዊነት፣ ለታላቅነትና ለጋራ እድገት፡፡
ምርጫችን ብልፅግና!