የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የጸና ወዳጅነት በመተማመን ላይ የተመሠረተ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በነበራቸው የሥራ ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ግርማዊ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር መወያየታቸውን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ግንኙነት "የጸና ወዳጅነት፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ትብብር!" ሲሉ ገልጸውታል።
ውይይታቸው በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ለረጅም ዘመናት የቆየውን ወዳጅነት ይበልጥ በማጎልበት፤ በትብብር እና በቀጣናዊ መረጋጋት ዙሪያ ላይ ያተኮረ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የፀና ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር ለተጋሩት የፀና አቋም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።