የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተጀመረ
ዛሬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በግምገማ መድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንደሻዉ ጣሰዉ(ዶ/ር)፣ የዋና ጽ/ቤት ከፍተኛ አመራሮችና የሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በመክፈቻዉ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት መድረኩ ፓርቲዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በዋና ዋና የፓርቲ ስራዎች ያከናወናቸዉን ተግባራት ይገመግማል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ የሚከናወነዉ ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ እንዲሆን በፓርቲዉ ሚናዎች ላይ በስፋት ይመክራል ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነዉም በልማት ተምሳሌት መሆን ችሏል ያሉት አቶ አደም ለዚህም የፓርቲዉ የአመራር ቁርጠኝነትና የህዝብ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንደሻዉ ጣሰዉ(ዶ/ር) በክልሉ ባለፉት ዓመታት የክልሉን ህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ ርብርብ በመደረጉ በርካታ ዉጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብ/ፓ/ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር) እንደተናገሩት ከሰዉ ልጆች ሁለንተናዊ ባህሪይ የሚነሳዉ ፓርቲያችን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋጥ ከህዝብ ጋር በመተባበር ቃልን በተግባር አረጋጠናል ብለዋል፡፡
መድረኩ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፡፡