በፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም የተሻለ መሆኑ ተመለከተ
"በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደ ሀገር ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ያስቀመጡት አቅጣጫ አፈጻጸም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሻለ መሆኑ በድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ቡድን ተመልክቷል።
የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ማጠቃለያ መድረክ የድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ቡድን ግኝቶችን በስፋት ገምግሟል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፥ በፓርቲያችን ፕሬዚዳንት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማሳካት በአመራር ቁርጠኝነትና በህዝብ ትብብር ርብርብ ተደርጓል።
በዚህም በሁሉም አካባቢዎች የኑሮ ውድነት ለማሻሻል፣ ከተረጅነት ለመላቀቅ፣ በኮሪደር ልማት፣ በዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ዙሪያ በየደረጃው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች የተሻለ አፈጻጸም በመመዝገቡ መልካም ልምዶች ተወስደዋል ብለዋል።
የተመዘገቡ ተሞክሮዎችን በማስፋፋትና ለእያንዳንዱ ግብ ባለቤት በማበጀት፣ ተቋማትን በማቀናጀትና ቀጣይነት ያለውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለበለጠ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባ አሳስበው በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮችና መሻሻል በሚገባቸው አፈጻጸሞች ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የፓርቲና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት መካሄድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ማጠቃለያ መድረክ ተጠናቋል።