የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት እና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለከተራና ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ጥር 10/2018 ዓ.ም
እንኳን ለ2018 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ጥምቀት ፍቅርንና ትኅትናን የምንማርበት ልዩ በዓል ነው። በሰማይም በምድርም የከበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ በፍጡሩና በአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ።
ኢትዮጵያ የልጆቿን እርስ በርስ መፋቀር፣ በአንድነትና በአብሮነት መኖር ዘወትር ትሻለች። ፍቅር ኃይላችን፣ አቅማችንና የአንድነት ካስማችን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ መምህረ ትኅትና ነው። በጥምቀት ፈጽሞ ያሳየን የትኅትና አምላክነቱን ነው። በፍጡሩ የሁሉ ባለቤትና ንጉሥ ሆኖ ሳለ በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ መጠመቁ ትኅትናን ሊያስተምረን ነው።
እኛም ትኁታን ልንሆን፣ ያለንበት ቦታ፣ የሀብት መጠን፣ የዝና ልክ፣ የኃይል ጥንካሬ ሳይወስነን ዝቅ ብለን ሕዝባችንን ልናገለግል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ጭቃ ነክተው፣ አፈር ረግጠው፣ አቧራዋን አራግፈው ወደ ልዕልና ለማሻገር የሚሠሩላትን ነው።
ኢትዮጵያም በትጉኃን ልጆቿ የብዙ ዓመታት መከራዋን እየገፈፈች፣ ሥር የሰደዱ ችግሮቿን እየፈታች፣ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሻገር ላይ ትገኛለች። ከዕዳዋ የሚልቀውን ሀብቷን እየገለጠች ወደ ምንዳ እየቀየረች ነው።
የጥምቀት በዓል ኢትዮጵያ በዐደባባይ የምትደምቅበት ውድ ጌጧ ነው።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን ኅብረረ ብሔራዊ አንድነታቸውን የሚገልጡበት ነው፡፡ ይህን የፍቅርና የአንድነት መገለጫና የዓለም ቅርስ የሆነውን በዓል ጠብቆ ማቆየት የእኛው ኃላፊነት ነው።
በድጋሚ መልካም በዓል!