ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምን አለዉ?
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የገበታ ለትውልድ ውጥን የተገነባው እና በ13.3 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምግብ ቤቶችን፣ የመዋኛ ገንዳዎችን፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገዶችን እና የሄሊኮፕተር ማረፊያን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት መገልገያዎች አሟልቶ ይዟል። በተጨማሪም በተለያዩ የፍራፍሬ ዞኖች እና ለዓይን በሚማርኩ አረንጓዴ ስፍራዎች የታጀበ በመሆኑ፤ ለጎብኚዎች የማይረሳ ትውስታን የሚሰጥ እጅግ ማራኪ ቦታ ነው።
ይህ ሪዞርት ከያዛቸው ዘመናዊ መገልገያዎች ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን ያላትን ቁርጠኝነት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቋሚ ምስክር ነው። የቱሪዝም ልማቱን ከተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ፣ ከዘላቂነት እና ከአካታችነት ጋር በማቀናጀት፤ ሪዞርቱ የወሎ ሕዝብ ያለውን ጥልቅ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴት ለዓለም ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቅበት ሰፊ ገበታ ሆኖ ያገለግላል።