የህዝብን ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት ርብርብ ማድረግ ይገባል - አቶ አደም ፋራህ
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በፓርቲና በመንግሥት መዋቅር ቅንጅት በገበያ ማረጋጋት እና ክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ በንቅናቄ የተሰሩ ተግባራት አፈጻጸም በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በመስጠት ተጠናቋል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በማጠቃለያ መድረክ ላይ እንደተናገሩት ገበያውን በዘላቂነት በማረጋጋትና
የህዝብን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት በመሰራቱ በዘርፉ አዎንታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ችግሮች ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመፍታት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብና ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት ርብርብ ማድረግ ይገባል።
ለዚህም ፓርቲው በአመራር ቁርጠኝነት ይሰራል፤ የፓርቲና የመንግሥት መዋቅርም ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
አቅርቦትን በማብዛት፣ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ብዛትና ጥራት በማሳደግ፣ የገበያ ማዕከላትን ጥራት በማጎልበት፣ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት አቅም በማጠናከርና አላስፈላጊ ኬላዎችን በማንሳት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ አደም አያይዘው እንዳነሱት በመደመር መንግሥት ዕሳቤ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መሰረት ያደረገ የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ስርዓት መከተል ይጠበቃል።
በዚህም በሁሉም ዘርፎች ያሉንን ዕድሎች አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የማምጣት ትልም ለማሳካት የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በተለይም የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት በሰለጠነ የሰው ኃይል የታገዘ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
ብዝሃ ተዋንያን መርህ ገቢራዊ በማድረግ የመንግስትና የግል ዘርፍ በቅንጅት በመስራት የስራ ዕድል ፈጠራን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ለተከታታይ ሶስት ቀናት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ሲካሄድ የቆየው የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የፓርቲ ስራዎችን በጥልቀት ገምግሟል። የተመዘገቡ አዎንታዊ አፈጻጸሞችን በማስቀጠልና ውስንነቶችን በማረም ለተሻለ አፈጻጸም መትጋት እንደሚገባም አጽንኦት ተሰጥቷል።