በወለጋ ያየናቸው የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጡ ናቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
በወለጋ የተለያዩ ዞኖች የተከናወኑ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ፣ በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የልማት ሥራዎችን ተመልክቷል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምዕራብ፣ በቄለም እና በምሥራቅ ወለጋ ዞኖች በተካሄደው የመስክ ምልከታ በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ የመስኖ ልማቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርታማነት የወለጋን ተፈጥሯዊ ጸጋ በሚያሳይ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም አርሶ አደሩ የሚያመርታቸውን እንደ በቆሎ፣ ሙዝና ማንጎ ያሉ ምርቶች ላይ ብክነትን ለመቀነስና እሴት ለመጨመር የሚያስችሉ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመር ትልቅ ተስፋ የሰጠ ሥራ መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጉብኝቱ ትኩረት ካደረገባቸው ቁልፍ ዘርፎች መካከል የሚከተሉትን ጠቅሰዋል፡-
- አርሶ አደሩና የገበሬዎች ዩኒየኖች ምርትን በማቀነባበር ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሸጋገሩ የተጀመሩ ሥራዎች፤
- ቱሪስቶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሚያስችሉ የኢኮ-ሎጅ ግንባታዎችና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች፤
- በነቀምቴ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ አዲስ ገጽታ ከመስጠቱም በላይ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
- ቀደም ሲል በአካባቢው ይስተዋል የነበረው የጸጥታ ችግር ተቀርፎ ማኅበረሰቡ፣ ሴቶችና ወጣቶች በሰላማዊ ሁኔታ ወደ ልማት ሥራ መሰማራታቸውን በጉብኝታቸው የተመለከቱ ሲሆን፤ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል።