በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ የብልፅግና ፓርቲ የልማት ዉጥኖችን ፍሬያማነት የሚመሰክሩ ስራዎች ተመልክተናል- የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ
ጥር 7/2018 ዓ.ም
የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
ከመድረኩ ጎን ለጎን በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች መጎብኘታቸውን አቶ አደም ፋራህ በይፋዊ የማህበራዊ ገፃቸዉ አስታውቀዋል።
በከተማዋ ዘመናዊነትን ከባህላዊ ትሩፋቶች ጋር በማጣመር ዘመናዊ የእግረኛ መንገድ፣ የአውቶብስ መጠበቂያ፣ ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች የተገጠሙለትና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማው የተገነባው የአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየምን የጎበኙ ሲሆን፥ ስታዲየሙ ወጣቶችን በስነምግባር አንጾ ለማሳደግና የስፖርቱን ዘርፍ ለመደገፍ እንዲሁም ፓርቲው በማህበራዊ ዘርፍ እየሰራ ለሚገኘው ስራ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።
ሀዲይ ነፈራ (የሀዲያ ደጃፍ) ተብሎ የተሰየመውን የታላቁ የሀዲያ ህዝብ ወግ፣ ባህልና የአኗኗር ዘይቤን አጣምሮ የያዘውን የባህል መንደር መጎብኘታቸውን ገልጸው፥ በተለያዩ አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ እየታዩ ላሉ መነቃቃቶች ሁነኛ ማሳያ እንደሚሆን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ እጅግ ባጠረ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃውን የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የጎበኙ ሲሆን፥ ስኬቱ በክልሉ ለሥራ ምቹ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት ለተያዘው ግብ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች የብልጽግና ፓርቲ የልማት ውጥኖች በአግባቡ ተግባራዊ ተደርገው ፍሬ እያፈሩ እንደሚገኙ ምስክር የሚሆኑ ናቸዉም ብለዋል፡፡
በአመራሩና በህብረተሰቡ የጋራ ጥረት እየተገኙ የሚገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ አደም ፋራህ ጥሪ አቅርበዋል፡፡