የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማድረስ ራዕይ ማሳያ ነው
በሁሉም የሀገራችን ከተሞች በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ የተተገበረው የከተማ ኮሪደር ልማት ዋና ከተማዋን ወደ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ሜትሮፖሊ ለማሸጋገር የታለመ ጉልህ የከተማ ልማት ውጥን ነው። የከተማ ኮሪደር ልማቱ በትራንስፖርት፣ መሠረተ ልማት፣ መኖሪያ ቤት እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር ግንኙነቶችን የሚያሳድጉ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚያጠናክር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ የነዋሪዎችን የኑሮ ጥራት የሚያሻሽል፣ በሚገባ የታቀደ እና የተቀናጀ ሆኖ ተተግብሯል፡፡ የኮሪደር ልማት ለከተማው እና ለሀገሪቱ በአጠቃላይ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አንድምታ አለው። የኮራደር ልማቱ የፓርቲያችን የመፍጠንና መፍጠር ስልት የተገበርንበት እና የልዕልና መር ህልማችን ያሳየንበት ቁልፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ በኮሪደር ልማቱ የህልማችንን የጥራት ደረጃ አሳይተንበታል፡፡ ፕሮጀክቱ ህብረትና አንድነት፣ ተስፋና ትጋት እንዲሁም የወል ህልም ፋይዳዎች በሚገባ አንጸባርቋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ መላው ኢትዮጵያዊያን እና ከተማችንን የጋራ ቤታቸው አድርገው የሚኖሩ አፍሪካውያን የኮሪደር ልማቱ ትሩፋቶች ተቋዳሽ ሆነዋል።
የኮሪደር ልማታችን የተለያዩ ተጨባጭ ፋይዳዎች አበርክቷል፡፡ ከእነዚህ አንደኛው የሀሳብና የተግባር ጥራት ከፍ ማድረጉ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሀሳብ ጥራትና የፕሮጀክት አፈጻጸም ደረጃ ላይ ማርሽ ቀይሯል፤ የኮርድር ልማቱ የተገነባበት የጥራት ደረጃ የብልፅግና ዓላማና ህልም በትክክል ይወከላል፡፡ ይህም ደረጃዋን ጠብቃ የምትገነባ ሀገርን ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባና እንደሚቻል ተግባራዊ ትምህርት እየተገኘበት ይገኛል፡፡
ሁለተኛው ፋይዳ አዲስ አበባ እንደ ስሟና የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲናነትዋ ወደሚመጥን የዘመናዊነት ደረጃ ከፍ ማድረጉ ነው። እንደሚታወቀው ከተማችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ከተማ ናት፤ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ ናት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ናት እንዲሁም ሦስተኛዋ የዓለምአቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች መናሀሪያ ናት፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ አዲስ አበባ በተፈጥሮና በታሪክ ጸጋዋ እንጂ በከተማ ጥራትዋ ተጠቃሽና ተወዳዳሪ ከተማ አልነበረችም፡፡ ዜጎቻችን ሌሎቹ የሀገራችን ከተሞቻችን ከአዲስአበባ የባሱ በመሆናቸው ብቻ ከሁሉም አቅጣጫ ይሰበሰቡባታል እንጂ ለሥራም ሆነ ለኑሮ ምቹ አይነበረችም፡፡ መሰረተ ልማቷና ገጽታዋ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷንና የዓለምአቀፍ ተቋማትና ዲፕሎማቶች መናሀሪያነቷን ፈጽሞ የሚመጥን አልነበረም፡፡ የኮሪደር ልማቱ ይህንን የቆየው ገጽታዋ በእጅጉ ያሻሻለና ተስፋ የፈነጠቀ ሆነ ተከስቷል፡፡
ሶስተኛው ፋይዳ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ልማት ደረጃ መቀየሩ ነው፡፡ በከተማ ልማት ዕሳቤ ውስጥ የከተማ ነዋሪዎች መብት/right to the city በተሰኘው ዕሳቤ ነዋሪዎች ከከተማዋ ማግኘት የሚገባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለ፡፡ የኮሪደር ልማቱ ይህንን ከማሟላት አንጻር አይነተኛ ሚና አለው፡፡
አራተኛው ፋይዳ የመንፈስ እርካታ ነው፡፡ ፓርቲያችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሳካት የሚጥር ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ለዜጎች ከቁሳዊ እርካታ ባሻገር ለመንፈሳዊ እርካታ ይሰራል፡፡ ዜጎች የቱንም ያህል ቁሳዊ ብልፅግና ቢያርጋግጡ የመንፈስ እርካታና ደስተኝነትን ካላገኙ ብልፅናቸው ሙሉ አይሆንም።
ከዚህ በተጨማሪ የከተማ ኮሪደር ልማት የሚከተሉትን ልዩ-ልዩ ጥቅሞች አበርክቷል፡-
• የከተማ እንቅስቃሴ እና ግንኙነትን አሳድጓል፡- የትራንስፖርት አውታሮችን የትራፊክ መጨናነቅን ቀንሷል፤ ዘላቂ መጓጓዣን እያበረታታ ይገኛል፡፡
• የኢኮኖሚ እድገትን እና ኢንቨስትመንትን ስቧል፡- የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመሠረተ ልማት፣ በንግድ፣ በሪል ስቴት እና በሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እየሳበ ይገኛል፡፡
• ጥቃቅናና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን አበረታቷል፡- የተሻሻለ መሠረተ ልማት የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪነትን አሳድጓል፡፡
• ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ደግፏል፡- ኮሪደር ልማቱ ከማዕከላዊ የንግድ አውታሮች ጋር አዋህዷል፡፡
• የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡- በግንባታ፣ በሪል እስቴት፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በእንግዳ ተቀባይነት እና በትራንስፖርት ከፍተኛ የስራ እድሎችን ፈጥሯል፡፡
• የመኖሪያ ቤት ዕጥረትን ፈትቷዋል፡- አዳዲስ የመኖሪያ ሕንጻዎች መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ተሰቷል፡፡
• የአስፈላጊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ተሻሽለዋል፡- የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና መገልገያዎችን ተደራሽነት አድገዋል፡፡
በርካታ ፋይዳዎችና ጥቅሞች እየተረጋገጡ ከዚህ በተቃራኒ የኮሪደር ልማቱ ትርፍና ቅንጦት አድርገው ማየት የሚፈልጉ አካላት ስለከተማ ልማትና የለማ ከተማ ስለሚኖረው ምንዳ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን በመረዳት ግንዛቤ ማሳደግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ ሆን ብሎ የሀገር እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነትን መጻረር ከሆነ ደግሞ አጀንዳው በመጣበት ልክ መታገልና ማምከን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ፕሮጀክቱ ልክ እንደ ህዳሴው ግድብ ስለራሱ የሚናገር እና ህዝብ የመሰከረለት በመሆኑ ተጻራሪ ሀሳብ ያላቸው አካላት ሀሳባቸው እየከሰመ እንደሚሄድ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ያለው የከተማ ኮሪደር ልማት ዋና ከተማዋ ዘመናዊ፣ የተገናኘች እና ሁሉንም ያቀፈች ዋና ከተማ እንድትሆን እድል ይፈጥራል። ይህ ጅምር በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ከሆነ አዲስ አበባን የአፍሪካ ግንባር ቀደም ከተማ እና የእድገትና የብልፅግና ማዕከል አድርጎ ሊያስቀምጣት ይችላል።