ኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮችን በስኬት እየተገበረች ነው - አቶ አደም ፋራህ
ኢትዮጵያ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮችን በስኬት በመተግበር ውጤት ማስመዝግቧን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የአፍሪካ ኅብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር የሆኑት የሌሶቶ ንጉስ ሌትሲዬ ሣልሳዊ በተገኙበት፣ በአፍሪካ የሕፃናት ዕድገትና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉት አቶ አደም ፋራህ፤ ኢትዮጵያ የሕፃናትን ጤናማ ዕድገት ለማፋጠን የሰቆጣ ቃል ኪዳንን፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ደግሞ የሌማት ትሩፋት እና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሮችን በስኬት እየተገበረች መሆኗን ጠቁመዋል።
በእነዚህ ሥራዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ እናቶችንና ሕፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል ብለዋል።
መንግሥት የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፣ የሀገር በቀል ፋይናንስን በማጠናከር እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈፀም ለአፍሪካ ብልፅግና መሠረት የሆነውን የሰው ኃይል በጋራ እናልማ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም (YADAM) ፋውንዴሽን መሥራች ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።