ብልጽግና ፓርቲን መምረጥ: ነጋችንን በዲጂታል ኢትዮጵያ ብሩህ ማድረግ ነዉ- አቶ ተመስገን ጥሩነህ
ብልፅግና ፓርቲን መምረጥ፤ ነጋችንን በዲጂታል ኢትዮጵያ ብሩህ ማድረግ መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ኢኒሼቲቮች የተገኙ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችም የኢትዮጵያን የመፈፀም አቅም ማሳያ መሆናቸዉንም ገልፀዉ፤ ብልፅግና ፓርቲ፤ ቀጣይነት ያለው እና በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አገልግሎትን ማስፋፋትን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ ማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ መልእክት ባስተላለፉበት ወቅት አቶ ተመስገን እንደገለፁት፤ ብልፅግና ፓርቲ ከትላንት የሚወሰዱ እሴቶች በአግባቡ በመገንዘብ፣ ሊወረሱ የሚችሉትን አምዶች በመለየት አዋጭ የሆነውን ቀጣዩን የኢትዮጵያ ጉዞ መተለሙን ጠቁመው፤ ይፋ የተደረገዉ የፓርቲዉ የምርጫ ማኒፌስቶ ይዘትም ይህንኑ መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለዲጂታላይዜሽን በሰጠው ልዩ ትኩረት እንዲሁም በዘርፉ ባከናወናቸው ስራዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አሰታዉሰዉ፤ አካታች የሆነ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓትን ከማረጋገጥ አኳያ ተጨባጭ እና ሰፋፊ ርብርቦችን እያደረገ እንደሚገኝ በማስታወስ ቀጣይነት ያለው እና በዲጂታይዜሽን የታገዙ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ከዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል እንደሆነም ተናግረዋል።
አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ከማድረግ ባለፈ እርስ በእርሳቸው ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የመስጠት ጅማሮዉም የዚሁ ማሳይ እንደሆነ አንስተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፌዴራል ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ፣ አሁን ላይ አገልግሎቱን ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደሮች መስፋፋቱንም አስታዉሰዋል።
የሰው ሀብት ልማት የዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንኑ ለማሳካት የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና መርሃ ግብር በሃገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ማድረጉንም ተናግረዋል።