ኢትዮጵያ ለዘመናት ብሔራዊ ክብሯን ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር የኖረችው በየዘመኑ በኖሩ አገር ወዳድ አባቶቻችን፣እናቶቻችን በከፈሉት ከፍ ያለ መስዋዕትነት መሆኑ የሚታወቅና ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ጀብድ ነው። አገር ሊወር ከሩቅ የመጣ ጠላት ጊዜው ያፈራውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስካፍንጫው ታጥቆና ውቅያኖስ አቋርጦ፤ በማንአለብኝነት ድንበር ጥሰው አንገታችንን ሊያስደፉን፣ኢትዮጵያዊ ክብራችንን ሊነጥቁን፣ሉዓላዊነታችንን ሊደፍሩ አስበውና አቅደው የመጡ ጠላቶቻችንን ኢትዮጵያ በኋላ ቀር መሳሪያ መክታና ድል አድርጋ የመለሰቻቸው በልጆቿ የተባበረ ክንድ ነው።
ኢትዮጵያዊያን በአዲስ ተስፋና በፈተና ውስጥ ናቸው። የያዝነው ተስፋ በግልጽ የሚታይ ነው፤ላለፉት ሃያ ሰባት የጨለማ ዓመታት በልዩነትና በጥላቻ አጥር ውስጥ ታጥረው የነበሩ ህዝቦቿ ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መገኘታችን ነው።
በህዝብ ስልጣኑን ተነጥቆ መቀሌ የመሸገው አሸባሪው የህወኃት ቡድን ያሳደገችውን፣ዘመናዊነትን ያስተማረችውን ፣አብልታና አጠጥታ ያሳደገችውን አገሩን ካላፈረስኳት ሙቼ እገኛለሁ በማለት ከሸሪኮቹ ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ውጣ ውረድ እዚህ የደረሰች አገር መሆኗን ያልተረዳው የጠላት ሃይል እሱ የገነባት ይመስል ካላፈርስኳት ሲል ቅዠቱን ያስተጋባል፡፡ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊያን እያሉ መቼም አትፈርስም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከውስጥም ከውጭም ካሉ ጠላቶቻችን ጋር እያደረግነው ያለነው ትግል ለአፍሪካዊያን አዲስ የተስፋ ብርሃን እንደሚፈነጥቅም ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡የኢትዮጵያ አሸናፊነት ቀድሞ የታያቸው ወዳጆቻችንን አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን እያሉ ሲሆን የኢትዮጵያዊያን ከመንግስታቸው ጎን በአንድነት መቆም ያስደነገጣቸው ኃይሎች ደግሞ ዛሬም ድረስ ከጠላት ጋር ወግነው አገር የማፍረስ ምኞታቸውን ለማሳካት በትብብር ሲሰሩ እያየናቸው ነው፡፡
ይህንን ቀድሞ የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ እኛ ልጆቿ እያለን አገር በጠላት ሃይሎች አትፈርስም በማለት ወደ ግንባር በመትመም ከሰራዊታችን ጋር ሆነው ጠላትን እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡
ይህ ዘመቻ ሀገር ለማፍረስ የታቀደውን ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት ተነስተን ጠላቶቻችንን የመመከትና ድል የማድረግ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብሯን የማስከበር ወሳኝ የህልውና ዘመቻ ነው።