ሁሉም ለአገሩ ሁሉን ነገር ሆኖ ሲቆም… /በአብዲ ኬ/

ሁሉም ለአገሩ ሁሉን ነገር ሆኖ ሲቆም… /በአብዲ ኬ/

  • Post comments:0 Comments
ዘንድሮ እንደ አገር የገጠመን ፈተና መቼም ከባድ ነው፤ መልከ ብዙም ነው፡፡ የእናት ጡት ነካሾች በአገራቸው ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ፤ የቅርብና የሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቻች ሳይቀሩ አጋጣሚውን ተጠቅመው ሊያዳክሙን፤ ከተቻለቸው ደግሞ እንደ አገር ህልውናችን አብቅቶለት እንድንበተን እየሰሩ ነው፡፡
እናት አገራቸውን ለሚወጉት ባናዳዎች ስንቅና ትጥቅ አቀባይ ከመሆን ባለፈ፤ ህዝቡ እንዲሸበርና ደህንነት እንዳይሰማው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዙ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው፡፡
ከሃዲውና አሸባሪው ህወሃትና ግብራበሮቹ ደግሞ በጦር ግንባር ከሚፈጥሩት ቀውስ ባለፈ፤ በየከተማው ሽብር የሚፈጥር፤ የነሱን አላማ የሚያራምድ አስተኳሽ በየቦታው ሰግስገዋል፡፡
ከስነ ልቦና እና የግንባር ውጊያ ባልተናነሰ፤ ኢኮኖሚው ላይ የተከፈተው ምዝበራና አሻጥርም ትልቅ አገር የማተራመስና የማዳከም ስልት ሆኖ በአሸባሪውና ላኪዎቹ እየተዘመተብን መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአገር ስም ማጠልሸትና ገጽታን ማበላሸትም እንዲሁ ሌላ ከጦር ግንባር ባልተናነስ አገር ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ግን፤ ይህ ሁሉ ፈተናና ዘርፈ ብዙ ጦርነት መንግስትና አመራሩ ላይ ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ቤት የሆነችው አገር ላይ የተከፈተ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ፤ ለእናት አገሩ ጠበቃ መቆሙ፤ ከእርሷ በፊት እኔን ብሎ ደረቱን ለመስጠት መዘጋጀቱ ለወገን ተስፋ የሚሰጥ ለጠላት ደግሞ ተስፋ የሚያጨልም ነው፡፡
ከጦርነቱ ጅማሮ አንስቶ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍና በተግባር የታየው ደጀንነት ሲታይ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ አካባቢውን በመጠበቅ፤ የተለዩ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት ለጸጥታ ሃይሉ በመጠቆም፤ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በቪዲዮ ጭምር በማስቀረት ሁሉም የጸጥታ ሃይሉን ሳይጠብቅ የአገሩ ጠባቂ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት በርካታ የጥፋት ድግሶች እየመከኑ፤ የጠላት ተላላኪዎች መፈናፈኛ እያጡ ነው፡፡ ጠላትም መግቢያ ቀዳዳ አጥቶ ተስፋ ወደ መቁረጥ እየሄደ ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ በአደባባይ ወጥቶ *እጃችሁን ከአገሬ ላይ አንሱ* እያለ ድምጹን እያሰማ ይገኛል፡፡ ባለው አቅም ሁሉ ከመንግስትና ከጸጥታ ሃይሉ ጎን ለመቆም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ነፍሱን ለመስጠት እንደማይሰስት በይፋ እየገለጸ ነው የሚገኘው፡፡
በውጭ የሚኖሩ የአገር ልጆችም ባላቸው አቅም ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ባለፈ ባሉበት ሆነው ለአገራቸው ድምጽ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ከአገር ልጆች አልፎም መላውን አፍሪካዊያንና ጥቁር ህዝቦችን የማስተባበር አቅም እያጎለበቱ ነው፡፡ በዚህም ተባብሮ የተነሱብን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ቆም ብሎ እንዲያስብ እየሆነ ነው፡፡
በእውነቱ ከሆነ ዛሬን ጨምሮ ከሰሞኑ በአገር ውስጥና በውጭ ያለው ዜጋና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንቅስቃሴ ልብ የሚያሞቅ ከመሆን ባለፈ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ሁሉን ነገር ሆኖ ለማገልገል ያለውን ዝግጁነት በግላጭ የሚያሳይ ነው፡፡

Leave a Reply