/በሚራክል እውነቱ/
ሰው ከቤቱ፣ ከቀዬው፤ ከተወለደበት፣ ካደገበት፤ ወልዶ ከከበደበት ቀዬ ሸሽቶ፤ ርስቱን ጥሎ ወዴት መሄድ ይችላል? ማይካድር የህወሓት ጁንታ ቡድን ትክክለኛ ማንነት የተገለጠበት የደም ምደር!! መላው የአገራችን ህዝብ በዚህ ቦታ በሆነው ልቡ ተሰብሯል፡፡ ህሊናው ደምቷል፡፡ አጥፊው የህወኃት ቡድን ለረዥም ዓመታት ተዋልደውና ተዛምደው የኖሩ ንጹሃን ላይ በማንነታቸው ምክነያት ጭፍጨፋ አካሄደ፡፡ ጊዜ የማይሽረው ጠበሳ፣ በዘመን የማይለወጥ የሀገር ክህደት በማይካድር ተፈጽሞ ተመለከትን፡፡ በርግጥም ስግብግቡ የህወኃት ጁንታ ቡድን ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር ጥርስ ተናክሷል፡፡ ለዚህም ነው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የንጹሃንን ደም ለማፍሰስ የማይዳዳው፡፡ ይሄው ጁንታ ቡድን ከህዝብና ከሀገር የዘረፈውን ገንዘብ ለጀሌዎቹ በማከፋፈል ሀገር ሰላም ውላ እንዳታድር፣ ህዝብን በብሔርና በጎራ በመከፋፈል እንዲጠፋፋና አንደነቱን እንዲያጣ ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ጉድጓድ ሲመስ ይውላል፡፡ ጁንታው የህውኃት ቡድን ወንጀለኛ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት ድርጊት ንጹሃንን በመረሸን በማይካዳር አሳይቷል፡፡ይህቺ ደሃ ሀገር ከጠላት ጠብቃ ያላትን አብልታ ባቆየች በሰራዊቱ ላይም ጥቃት በመሰንዘር ጡት ነካሽነቱን በተግባር አሳይቷል ፡፡ሀገር ሰላም እንድታድር በበረሃ በጫካ የሚያድረውን፤በኢትዮጵያ ክብር የማይደራደረውን የአገርና የህዝብ ደጀን ወታደር ላይ አፈ ሙዝ በማዞር የጭካኔውን ጥግ አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በሀፍረት አንገት ያስደፋ፣ የወለደች እናትን ለምለም ማህጸኗን ያስረገመ፣ ወንጀል ሰርቶ ብሔሩን መሸሸጊያ ያደረገ ባንዳ የፈጸመው ድርጊት መቼም ከታሪክ ማህደር የማይፋቅ እኩይ ተግባር ሆኖ ይመዘገባል፡፡ዜጎችን በማንነታቸው ምክንያት ለመበታተን ቢጥሩም ዘርና ጎሳን አስቆጥረው ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ለማውረድ ቢሞክሩም ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ግን ዛሬም እንደትናንቱ እንደጠነከረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በላይ ለመብታቸውና ለማንነታቸው፣ ከሀይማኖት አባቶች በላይ ስለሀይማኖታችሁ እናውቅላችኋለን ሲሉ ዘመናትን የህዝብ ጫንቃ ላይ ተንጠልጥለው የኖሩት እነኚህ የባንዳ ስብስቦች ዛሬ ደግሞ ይባስ ብለው ሉዓላዊነትን የተዳፈረ ድርጊት ፈጸሙ፡፡በነጻይቱ ሀገር ተወልደን በዘርና በጎሳ ጠበን እንድንሞት የሚፈልገው ስግብግቡ የጁንታ ቡድን ፍላጎቱ ተሳክቶ ማየት አልቻለም፡፡ ለዚህም ነው እዛና እዚህ ጦር እየሰበቀ ነጋሪት እየጎሰመ ሀገርን ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚሰራው፡፡ ይሁንና የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከእውነትና ከፍርድ የሚቀር አንድም የለምና ይህ አጥፊ ቡድን ለዘመናት በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ግፍና መከራ፣ እንግልትና ስቃይ፣ አምባገነናዊነትና ጸረ-ዴሞክራሲያዊነት እንዲሁም ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ከፍትህ ፊት ቆሞ ኢትዮጵያውያን ቀና ብለው የሚሄዱበት ቀን በቅርቡ እውን ይሆናል፡፡ ትናንት ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጸም ምንም የምህረት ልብ የሌለው አካል ዛሬ በፍትህ ፊት ቆሞ እውነትን ከያዙት ኢትዮጵያውያን ጋር ይፋለማል፡፡ ኢትዮጵያም እንደጠነሰሱላት ሴራ ሳይሆን በቁርጠኛ ልጆቿ መስዋዕትነት ከፍታው እውን ይሆናል፡፡ ደስ ይበልሽ ሀገሬ! ዛሬም ለከፍታሽ መስዋዕት የሚሆን እልፍ ኢትዮጵያዊ በእቅፍሽ ነው! ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !