ወንጀለኛው የሕወሓት ጁንታ ቡድን የሰራው ግፍ በውጭ ሚዲያዎች ሊሸፋፈንለት አይገባም!

ወንጀለኛው የሕወሓት ጁንታ ቡድን የሰራው ግፍ በውጭ ሚዲያዎች ሊሸፋፈንለት አይገባም!

  • Post comments:0 Comments

/ፍኖተ አዲስ/

የአገር ክህደት ወንጀል በፈጸመው የጁንታው ህወሓት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግንና ስርዓትን የማስከበር ዘመቻ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች የሚዘግቡበት መንገድ በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባው እኩይ ድርጊት ነው፡፡ አሶሴትድ ፕሬስን ጨምሮ በተለይ ቢቢስ ኒውስ በሰሞኑን ዘገባው በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሀይል እርምጃ እየተወሰደ ነው ብሎ ያቀረበው ዘገባ የአገር ክህደት ወንጀል በፈጸመው የህወሀት ጁንታ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለ ህግንና ስርዓትን የማስከበር ዘመቻ በሚል መታረም ያለበትና ዘገባው የኢትዮጵያ መንግስትን የማይመለከት ለአንድ ወገን ብቻ ያደላና የጋዜጠኝነት ህግና ስርዓት ያለተከተለ ብኩን ዘገባ ነው የሚል እይታ አለኝ፡፡ቢቢሲ ኒውስ በሰራው ዘገባ ህግን የማስከበሩን ሂደት ከኖቤል ፕርይዝ ሽልማቱ ጋርም ለማያያዝ ሲሞክር ታይቷል፡፡ ይህ ሚዲያ በዘገባው የባለፈው ዓመት የኖቤል አሸናፊው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በትግራይ አመራሮች ላይ ድብደባ እያካሄደ ነው የሰላም ውይይቱንም አልቀበልም አለ ሲል ዘግቧል፡፡ አገርን ከወንበዴዎች መታደግ ከኖቤል ሽልማት ጋር የሚያገናኘው ነገር ሊኖርም አይችልም፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ አገር ይቀድማልና፡፡‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ›› በሚል መርህ ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ከልክ በላይ ወንጀለኛውን የህወሀት ቡድን ሲታገሰው መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ግፍ ትተን በዚህ ሁለት አመት እንኳ ህገ ወጥ ድርጊት ውስጥ ሲዘፈቅ መንግስት በማስታመም የሰላምን መንገድ ሲከተል ቆይቷል፡፡ ወንጀለኛው ቡድን በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ሲከሰቱ የነበሩ ግድያዎችን፣ የጸጥታ ችግሮችን ከጀርባ ሆኖ በፋይናንስ ጭምር በመደገፍ ለመንግስትና ለሀገር ከፍተኛ ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከህግ ባፈነገጠ መልኩ ምርጫ በማካሄድ የመንግስትን ትእግስት ተፈታትኗል፡፡ ይሄን ሁሉ ሲያደረግ ለበርካታ አመታት በጦርነት የተሰቃየው የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ በሚል መንግስት ሲታገሰው ቢቆይም ለኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ የሆነውንና ለጎረቤት አፍሪካ አገራት ጭምር የሰላም ተልዕኮ ኃላፊነቱን በሚገባ ሲወጣ የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ህግና ታሪክ ይቅር የማይለውን እኩይ ድርጊት ፈጸመ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የግፍ ጽዋው ሞልቶ መንግስት ወደ ህግ ማሰከበሩ የገባው፡፡ የውጭ ሚዲያዎች ይሄንን ሀቅ ነው መዘገብ ያልቻሉት ወይም ያልፈለጉት፡፡ መንግስት ህግን የማስከበር ተግባሩ እንደውም በመዘግየቱ ሊወቀስ ይገባው እንደሆን እንጅ 110 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ የደገፈውን የህግ ማስከበር ተግባር የውጭ ሚዲያወች ሊኮንኑት አይገባም ነበር፡፡በአንድ ወቅት የችችኒያ አማጺዎች ሩሲያን እንዳልነበረች ለማድረግ ቆርጠው ተነስተው ነበር ከዚያም የሩሲያ መንግስት ሀገሪቱን ከጥፋት ለማዳን በእነዚሁ አማጺዎች ላይ መረር ያለ እርምጃን መወሰድ ሲጀምር አለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰብዓዊነት ተረገጠ እያሉ ያስተጋቡ ጀመር ነገር ግን የሩሲያ መንግስት ህግን እያስከበረ ነበርና ሀገሪቱን ዳግም ከመበታተን ጠብቆ ታላቅ ሀገር ማደረግ ቻለ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም ይሄንን ነው እያደረገ ያለው፡፡ እዚህ ላይ የሩሲያው መንግስት ትላንት ስለአገራችን የተናገሩትን ማንሳት ጥሩ ይመስለኛል ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው ጦርነት ሳይሆን ወንጀለኝነትን በመቆጣጠር ህግን ለማስከበር የሚደረግ ትግል ስለሆነ ሀላፊነቱ ሀገሪቱን የሚመራት መንግስት ብቻ ነው፡፡ ጣልቃ በመግባት ለማደራደር የሚፈልግ የውጭ ሀይል አሸባሪውን የወንጀለኛ ቡድን እንደመደግፍ ይቆጠራል›› ነበር ያሉት፡፡ እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚል አስተሳሰብ የተለከፈው ወንጀለኛው ቡድን እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ሊያስብ ቀርቶ ከአብራኩ የተገኘውን የትግራይ ህዝብ ሲበድልና ሲያሰቃይ የኖረ ቡድን ነው፡፡ ለ45 ዓመታት የትግራይ ህዝብ እንዳይናገር ተደረጎ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሰቃይ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ይህን ሀቅ ነው ሚዲያዎች መዘገብ ያለባቸው፡፡ የታሪክ አተላው የህወሀት ጁንታ ቡድን ህግና ታሪክ ይቅር የማይለውን ተግባር በሰሜን እዝ ላይ መፈጸሙ ሳያንሰው ምንም ውስጥ የሌሉበትን በርካታ ንጹሀንን በማይካድራ ጨፈጨፈ ይህን ሁሉ አድርጎ አሁንም እነርሱ እየተበደሉ እንደሆነ የውሸት ፕሮፓጋንዳዎችን በቀዳሚነት በመልቀቅ የአለም ማህበረሰብን ሲያወናበዱ ይስተዋላል፡፡ ይሄን ያደረጉትን ዘግናኝ ጉዳይ በእኛ በኩል ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ መግለጽ ላይ ክፍተት ይታይል፡፡ ይሄን ነውር ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ መግለጽና ህወሀት ሰይጣን እራሱ የሚቀናበት ወንጀለኛ ጁንታ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ የቀጣይ የቤት ስራችን ነው፡፡ ወንጀለኛውን የህወሀት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ህግ ለማቅረብ እየተደረገ ባለው ተጋድሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆሙን መቀጠል ይገባዋል፡፡ ህግ የማስከበሩ ስራም ወንጀለኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህግ በማቅረብ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ጁንታ ለህግ መቅረቡ የትግራይን ህዝብ ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ የትግራይ ህዝብ በቃህ ሊለው የሚገባው ጊዜም አሁን ነው፡፡በፈረሰች ሀገር ውስጥ ጋዜጠኝነት ሊኖር አይችልምና አገር ለማፍረስ ያልተገባ መረጃ በመስጠት ሌላ ክህደት የምትፈጽሙ ግለሰቦች ከድርጊታችሁ ብትቆጠቡ መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በውጭ ሚዲያ ላይ የምትሰሩ ሪፖርተሮች ወይም ኮሮሰፖንዳንቶች የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደው ያለው እርምጃ አገርን የመታግና ህዝብን የማስከበር መሆኑን አለም እንዲያውቀው ማድረግ ይገባል፡፡ ዘላቂ ሰላም የሚመጣው ወንጀለኞችን በመቅጣት ብቻ ነው!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

Leave a Reply