ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ በልጆቿ ብርታት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ማንም የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ከአገርም ሆነ ከሕዝብ ሊያስበልጥ አይችልም፡፡ የትኛውም ሃይል ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ሊያወርደን አይደለም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እንዲያደበዝዝ አንፈቅድለትም፡፡
ምክንያቱም ሃገር ከምንም ትልቃለች፡፡ በሃገራዊ አንድነት ጥላ ስር ተሰብስበን ለሃገራዊ ለውጥ የምንተጋበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ቃል በመፈጸም በህዝብ ዘንድ የተጣለበትን እምነትና አደራ ይወጣል፡፡
ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን ከወንድማማችነት ይልቅ ልዩነትን የሚያቀነቅኑ ሃይሎች በብልጽግና ዘመን ቦታ የላቸውም፡፡
ብልጽግና ሕብረ-ብሔራዊ ሆና በተገነባች ኢትዮጵያ ላይ አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግ አካሄድ መቼም አይከተልም፡፡ ይህን ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች ካሉም በጽናት ይታገላል፡፡ የፓርቲው ፕሮግራምና ህገ ደንብ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለተግባራዊነቱ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳያል፡፡
ብልጽግና የኢትዮጵያዊነት ባህሪን የያዘ ህዝባዊ ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ማለት እርስ በእርስ መተሳሰብን፣ መተጋገዝን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን የመሰሉ የቆዩ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የሚሰራ ወቅቱን የዋጀ ፓርቲ ነው፡፡
አመራሩም ሆነ አባሉ እነዚህን ኢትዮጵያዊ እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ ተጥሎበታል፡፡ ከእዚህ አኳያ አመራሩም ሆነ አባሉ በፓርቲው ፕሮግራምና ህገ ደንብን ተከትሎ የሚመራ ይሆናል፡፡
ለዘመናት በተካሄደ ትግል በልጆቿ በተገነባች ኢትዮጵያ ውስጥ በዴሞክራሲና በነፃነት እየኖሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ከማድረግ እና የብልጽግና ጉዟችንን ከማፋጠን ይልቅ ከውስጥም ከውጭም በባዕዳን ነዋይ ተደልለው በገዛ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የጸረ-አንድነት መፈክር በማሰማት ህዝብ የሚፈልገውን አገራዊ ዕድገት ለማስተጓጎል ጥረቶችን አድርገዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጎልበት ለእንደዚህ አይነቱ ተራ የእልቂት ነጋሪት ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ጥላቻን በጥላቻ ሳይሆን ማሸነፍ የሚቻለው ጥላቻን በፍቅር እንደሆነ ብልጽግና ፓርቲ ያምናል፡፡ ይህ ደግሞ ፓርቲው በህዝብ ዘንድ የገባውን ቃል ለመወጣት ያግዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረውን ፍቅር፣ መከባበርና መደጋገፍ እንደገና ወደነበረበት በማስቀጠል አንዱ ጎታች ሌላው ተጎታች ሳይሆን ወይም አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሳይሆን ሁሉም እኩል ለሀገሩ ብልፅግና አሻራውን የሚያሳርፍበት ወቅት እንዲሆን ፓርቲው ፕሮግራሞቹንና ህገ ደንቦቹን ተከትሎ እየሰራ ይገኛል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ከሰራቸው ስራዎችና ካመጣቸው ለውጦች ይልቅ ገና ወገብ የሚያጎብጡ ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውጤት ለማምጣት ርብርብ እያደረገ የሚገኝ ፓርቲ ነው፡፡ ምክንያቱም ብልፅግና በዕውቀትና በዕውነት ላይ የቆመ ፓርቲ ነውና፡፡ ብልጽግና ህልሙ ትልቅና ሰፊ እንጂ በትንንሽ ነገሮች ረክቶ የሚቀመጥ ፓርቲ እንዳልሆነ ካስቀመጣቸው ፕሮግራሞችና ህገ ደንቦች መረዳት ይቻላል፡፡
አገራዊ አጀንዳን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ከማንም የተደበቀ አጀንዳ የለውም፡፡ አጀንዳው ልማት ነው፡፡ ብልጽግና ነው፡፡ ትንንሽ ልዩነቶቻችንን በማቻቻል፣ ከጎጠኝነትና ከቡድንተኝነት አስተሳሰብና ድርጊት በመውጣት እና ለሃገርና ለሃገራዊ አንድነት ቅድሚያ መስጠት ከቻልን በእርግጥም የበለጸገች ኢትዮጵያን በጋራ ድካማችን መገንባት እንችላለን፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ነገን ተሻግሮ ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ዛሬን እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ፓርቲው ለአገርና ለህዝብ የማይከፍለው መስዋዕትነት የለም፡፡ ምክንያቱም ሀገር ከሁሉም ትልቃለችና፡፡