You are currently viewing የህግ የበላይነት መረጋገጥ ለሀገራዊ ብልጽግና /በሚራክል እውነቱ/

የህግ የበላይነት መረጋገጥ ለሀገራዊ ብልጽግና /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments
እኛ ኢትዮጵያዊያን “በሕግ አምላክ” ከተባልን ደንገጥ ብለን ከድርጊታችን መቆጠባችን አይቀርም፤ቆም ብለን የምንባለውን ማድመጣችን ለሕግ አክባሪነትና ለህግ ያለንን ተገዢነት አመላካች ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ትልቁ ጥቅም ፖለቲካዊ መረጋጋትን መፍጠርና የሕዝብን በሰላም መኖር ማረጋገጥ ነው፡፡
ሰፋፊ የቢዝነስ ስምምነቶችና ስራዎች የሚከናወኑት የሕግ ጥበቃና ከለላ ሲኖር እንደመሆኑም ለኢኮኖሚ እድገቱም ቢሆን አበርክቶው የማይተካ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር፣ የመንግስትና የግል አካላት ብሎም ማህበራት በመተማመን ስሜት በጋራ ይሰራሉ፡፡ ሕግ በሰዎች ፍላጎት እንዳይጠመዘዝ በማድረግ የተሻለ ማህበራዊ አገልግሎትና ፍትህ ለመስጠትም ያስችላል፡፡በጥቅሉ የህግ የበላይነት መከበር ጠቀሜታው በእጅጉ የጎላ ነው፡፡
የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ከሰው ልጅ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ የህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ጋርም ይያያዛል፡፡ ስለዚህ በአንድ አገር የሕግ የበላይነት ተረጋገጠ ማለት፤ አንድ ሰው ንግድ ሲሰራ ትርፍና ኪሳራውን እንደሚያውቀው ሁሉ፤ አንድ መንግስትም የህግ የበላይነትን አስከብሮ ዜጎቹን በሕግ ሲመራ የህዝቡን ስሜት ተቆጣጥሮ ለመጓዝና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር ያስችለዋል፡፡
የሕግ የበላይነት ካለ ነጻነት መኖሩ አይቀሬ ነው፤ የበላይና የበታች የሚባል አካል ስለማይኖርም በህግ ፊት ሁሉም እኩል የሚሆንበትን እድል ስለሚፈጥር የዜጎችም እኩልነት ይረጋገጣል ማለት ነው፡፡
በተመሳሳይ ሕግ የበላይነቱን ሲይዝ አጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚ ላይም አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ምክንያቱም የሕጎች ተገማች መሆን ኢኮኖሚውን ያበረታታል፤ ልማትን ያፋጥናል፤ ግጭቶችን በመቀነስም ኢንቨስትመንትን ያነቃቃል፡፡ ከዚህ ባለፈም፣ የህግ የበላይነት ሲኖር፣ የጎበዝ አለቃ አይፈጠርም፤ ስርዓት አልበኝነትም አይኖርም፡፡ በጥቅሉ፣ የሕግ የበላይነት መኖር ለሰው ልጅ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ለፍትህና የመንግስትን ስልጣን ለመቆጣጠር ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለአገር ግንባታ መሰረት ነው፡፡
በአንድ አገር የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የሕግ የበላይነት የራሱ ሂደት አለው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው በአንድ ሌሊት ሳይሆን በሂደት፤ ለዚህ መከበር የሚሰሩ ተቋማት እየተገነቡ ሲሄዱም ነው፡፡
በሌላ በኩል የሕግ የበላይነት ካልተከበረ በጭራሽ የሰው ልጅ ነጻነትና እኩልነት አይከበርም፤ አጠቃላይ የአገር እኩልነት፣ ነጻነትና ፍትሃዊነት ጉዳዮች ላይ ገደቦች ይወድቃሉ:: ከዚህ ባለፈም የሕግ የበላይነት ከሌለ የጎበዝ አለቃ ስለሚበዛ አለመረጋጋት ይፈጠራል:: የህዝቦችን ማህበራዊ ሕይወት ያናጋል፤ ተቋማትን ያዳክማል፤ የአገርን ኢኮኖሚም ይጎዳል፡፡
ለምሳሌ፣ አንድ ሰው በአንድ ቦታ ኢንቨስት ለማድረግ ቢፈልግ፤ የሕግ የበላይነት ስላለ ለሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ ጥበቃ አለኝ፤ ማንም መጥቶ አይቀማኝም፣ ንብረቴን አይጎዳብኝም ብሎ ማመን ይኖርበታል፡፡ በዚህ መልኩ በሚፈጠር መተማመን ኢንቨስትመንቱ እንዲያድግ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋል፤ ህብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የሚችልበት እድል ሊፈጠር ይገባል፡፡ ሆኖም የሕግ የበላይነት ከሌለ፣ ማንኛውም ሰው ተነስቶ ሰውን ይጎዳል፤ ይገድላል፤ ንብረት ይቀማል፤ ያፈናቅላል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ እንደ ሀገር የህግ የበላይነትን በማስከበር የሚገኘውን ሀገራዊ ትርፍ እና ከዚሁ ጎን ለጎን ሰላሟ የተጠበቀና በኢኮኖሚ ያደገች በሁለንተናዊ መልኩ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ብሎም ደህንነታቸው የተጠበቁ ዜጎች የሚንቀሳቀሱባት ሀገርን ለመፍጠር የህግ የበላይነት ማስከበርን አብይ አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ከዚህ የምንረዳው ብልጽግና ፓርቲ በህግ የበላይነት ላይ ምንም አይነት ድርድር እንደማያደርግ ነው፡፡
ህብረ ብሔራዊነትን ማጎልበት፣የወንድማማችነት እሴትን ማሳደግና መጠበቅ፣ዜጎች በዜግነታቸው ክብር የሚያገኙበት በማንነታቸው የማይሸማቀቁበት እንዲሁም በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ኢትዮጵያዊ ምድርን ለመፍጠር ከተፈለገ የግድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ለዛም ነው ብልጽግና ፓርቲ ከውስጥም ከውጪም በሚገጥሙት ፈተናዎች እጅ ሳይሰጥ ህዝብን ማዕከል ያደረገ የህግ የበላይነት የማስከበር ስራውን እየሰራ ያለው፡፡ብልጽግና እንደ ፓርቲ ሆኖ ማየት የሚፈልገው ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ስርዓትና ሀገር መፍጠር ሳይሆን የህግ የበላይነትን የተረዳና ለህግ ተገዢ የሆነ ማህበረሰብ ተገንብቶ ማየት ነው፡፡
ባጠቃላይ ሕግ የበላይነቱን ሲያጣ በህብረተሰቡ ውስጥ የተረጋጋ የማህበራዊ ሕይወት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ይፈጥራል፤ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና ውድቀትን ያመጣል፡፡ በመሆኑም የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ለአንድ አገርና ህዝብ ትልቅ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የህግ የበላይነት ተረጋግጦ በጋራ ርብርብ የምንሻትን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መላው ኢትዮጵያዊያን የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል እላለሁ፡፡ ሰላም !

ምላሽ ይስጡ