በተለያዬ ቦታ ብንሆንም የተሳፈርነው በአንድ ጀልባ ነው  /በሚራክል እውነቱ/

በተለያዬ ቦታ ብንሆንም የተሳፈርነው በአንድ ጀልባ ነው /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

በአሁኑ ሰዓት የሰላም መሰረቶችን ለማጠንከር ከሚሰሩ ስራዎች ባሻገር የወንድማማችነት እሴት እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጦት እየተሰራ ነው፤ብልጽግና ፓርቲ ስብራቶችን የሚጠግንና ሽንቁሮችን የሚደፍን ጠንካራ የፖሊሲ ሀሳቦችን ያቀረበ ፓርቲ በመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ከፓርቲው ጎን በመቆም ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

መላው የአገራችን ህዝቦች የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን በብቃት በመመከት አገራችን የጀመረችውን የለውጥና የከፍታ ጉዞ በጽናት በማስቀጠል ብሎም የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም፣ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ብሄራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ ፓርቲው ባለፉት አራት የለውጥ አመታት በየደረጃው ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል::

ፓርቲያችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን፣ አብሮነትን፣ የአንዱ ስኬት የሌላው ስኬት፣ የአንዱ ህመም የሌላው ህመም እንደሆነና እድልና እጣፈንታችንም አንድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ የፖሊሲ ሀሳቦችን በማቅረብ እንደ አገር ቀላል የማይባሉ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል፡፡

እንደ ሀገር ያደሩ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑ ባያጠያይቅም ከሚፈለገው ደረጋ ደርሶ ለማዬት ግን የሁላችንም ርብርብና ገደብ የለሽ ተሳትፎ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ በእርግጥ ችግሮቹ በአንድ ጀንበር የማይፈቱ ግን ደግሞ መጪው ግዜ ብሩህ ተስፋ የሚታይበት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ከእውነት ጋር መጋፈጥ መርሆው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ብልጽግና ችግርን በመሸሽ ሳይሆን ችግርን አውቆ በማከም ላይ ተመስርቶ እየሰራ ይገኛል ፡፡

የብልጽግና እሳቤዎች ጥልቅ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገሩ፣ እውነትንና እውቀትን መሰረት ያደረጉ፣ የችግሩን መሰረት በጥልቀት የሚፈትሹና ለኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ሁነኛ  መፍትሄዎች በመሆናቸው ህዝቡ እነዚህን ሀቆች አውቆ ከፓርቲው ጎን መሰለፍ ይኖርበታል፡፡

አብሮነታችንን ለማጠናከር፣ ወንድማማችነትን እውን ለማድረግ፣የእርስ በእርስ መተሳሰባችንን ለማጎልበት ብሎም እንደ አገር የደረሰብንን ፈተናም ሆነ የሚደርስብንን ጫና መሻገር የምንችለው ልክ እንደ አባቶቻችን በአንድነት መሰረት ላይ መቆምና መጽናት ስንችል ብቻ ነው፡፡

ወንድማማችነት ጓደኝነትን፣መተሳሰብን እና መተማማንን በውስጡ ይዟል።ጓደኝነት መተዋወቅንና መቀራረብን ያሳያል። መተሳሰብ ደግሞ በደስታና በሀዘን ወይም በችግርና በምቾት ጊዜ መደጋገፍን ያሳያል። መተማመን በጓደኝነት እና በመተሳሰብ ላይ ይመሠረታል። የሦስቱ ድምር ደግሞ የወንድማማችነት እሴት ይባላል፡፡ ወንድማማችነት የጋራ ራዕይ ያላቸዉን ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ማህበረሰቦችን በፍቅር ያስተሳስራል።

ወንድማማችነት አሁን ላይ ዓለም አቀፍ እሴት ሆኗል። በተጨባጭ ሲታይ ዓለም አንድ መንደር ወደ መሆን ተቃርባለች። ሀገራት ግንኙነቶቻቸዉን በወንድማማችነት ላይ እንዲመሠርቱ ይመከራል። ችግርም ሆነ ልማት በፍጥነት ከአንድ አከባቢ ወደ ሌሎች አከባቢዎች ሊዛመት ይችላል። ዛሬ ላይ በዓለም ደረጃ ወንድማማችነት ምርጫ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ሆኗል። የዓለም ማህበረሰብ የአንድ አከባቢ ህዝብ በተፈጥሮ ወይም በሰዉ ሰራሽ ችግር ሲጠቃ ለእርዳታ የሚረባረበዉ ለዚህ ኖሯል፡፡

አባቶቻችን ወንድማማችነትን ትርጉሙን ከፍ አድርገው አሳይተውናል፤ለወገናቸዉ ነፃነት እና ክብር ሲሉ በጀግንነት ተሰውተዋል። ሌላዉ ወገናቸዉ በክብር ይኖር ዘንድ እነሱ አለመኖርን መርጠዋል። ወገናቸዉ ይበላ ዘንድ እነሱ ተርበዋል፤ ይህን ውድ ማስዋዕትነት ያስከፈላቸዉ ጥልቅ የወንድማማችነት ስሜት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የዚያ ዘመን የወንድማማችነት አሻራ ዛሬ ላይ የደበዘዘ ቢመስልም በጋራ ርብርብ ማድመቃችን ግን አይቀርም።

ወንድማማችነታችን የቆዬ የኢትዮጵያዊነት መገለጫችን በመሆኑ ፈጽሞ ሊጠፋ አይችልም፤ምንም እንኳ እንደ አያያዛችን የሚወሰን ቢሆንም፡፡ ለዚህ ደግሞ ማሳያው ወንድማማችነት እየተገፋ፣ ፅንፈኝነት እያቆጠቆጠ መታየቱ ነው፡፡ ፅንፈኝነት ለአንድ ዓላማ ተመሳሳይ ነገር እያወራን እንኳ እንዳንደማመጥ አድርጎናል። ሁሉም ራሱን ብቻ የሀገር ምሰሶ አድርጎ ሌላዉን ላለመስማት ይዳዳል። በፅንፈኝነት ምክንያት ተናጋሪ በዝቶ አድማጭ ጠፍቷል።

ለዚህ ሁሉ መልስ ሁላችንም በወንድማማችነት ስሜት መደመር ነው። የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ወንድማማችነትን ይፈልጋል። አብዘኞቹ ችግሮቻችን የጋራ መሆናቸዉን በድፍረት መናገር ይቻላል። ኋላቀርነትን፣ ድህነትን፣ የተቋማት ድቀትን፣ ፅንፈኝነትን፣ ስንፍናን፣ ሌብነትን እና ሌሎች መሰናክሎችን በማለፍ ወደ ብልፅግና መዝለቅ የምንችለዉ በመተሳሰብ እና በመተማመን አቅሞቻችንን ስንደምር ብቻ ይሆናል። ይህ የወንድማማችነት እሴትን ማጎልበት ይጠይቃል። ፅንፈኝነት እና ዋልታ-ረገጥነት የህብረት ክንዳችንን ከማዛል ባሻገር ሊያጠፋፋን ይችላል፡፡

በተለያዬ ቦታ ብንሆንም ሁላችንም የተሳፈርነው በአንድ ጀልባ በመሆኑ የአንዱ ስፋራ ቀዳዳ ካልተደፈነ ሁላችንም ያሰምጠናልና ሁላችንም ተባብረን ጀልባችንን እንታደግ፡፡

Leave a Reply