በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ “ጽንፈኝነትና አክራሪነት የሰው ልጆች በሰላምና በነጻነት ኑሯቸውን መምራት እንዳይችሉ፤በሕዝቦች ዘንድ እንዲሁም መከባበርና መቻቻል እንዳይኖር መሰናክል የሚሆን አስተሳሰብ እና ተግባር ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት በኢትዮጵያ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ያሉ ባህላዊ የዕርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል ።ነገን የተሻለ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገር ወዳድነት ስሜት የሚችለውን ሁሉ አዎንታዊ ሚና መጫወት ይኖርበታል።
ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራና ዘላቂ ብሄራዊ መግባባት እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀርም። በመመካከርና በመነጋገር ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የቆዩ የቁርሾና ቂሞች በልማትና ዕድገት ላይ እያሳደሩ ያሉ ማነቆዎች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት ያስችለናል።
ለዚህም ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለት ግብ እንዲመታ በየማህበረሰቡ ዘንድ የሚገኙ ባህላዊ የዕርቅና ሰላም ግንባታ እሴቶች ተሞክሮ መውሰድና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ጥርጥር የለውም።ሀገሪቱ ላሉባት ችግሮች በዘላቂነት እልባት መስጠት የሚችል እንዲሆን የሁሉም ዜጎች ሀሳብና ተሳትፎ መረጋገጥ የሚገባው ሲሆን ለሂደቱ ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላትና ዜጎች አስተዋፅኦ አስፈላጊ ነው።
በተለይም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የተጣለባቸውን አደራ በብቃት መወጣት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለተሳትፎ ዝግጁ መሆንና ከውይይቱ የተሻለ ነገን ማየት እንደሚቻል አምኖ መግባት ለሂደቱ ስኬታማነቱ ይበጃል።
እኔ ከማለት እኛ በማለት ጫፍ ከወጣ ግላዊነት ይልቅ ሀገራዊ ማንነትን በማስቀደም የመፍትሔ ሀሳብ ይዞ መቅረብና መመካከር ይገባል። ለብሔራዊ ምክክሩ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች ተሞክሮ በመውሰድ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ያስችሉናል።
ሁሉም ዜጋ በየአከባቢያቸው ያሉ የእርቅና የሰላም ግንባታ እሴቶች የህይወት ሂደታቸውን የሚመሩበት መንገድ አድርጎ የሚቀበለው በመሆኑ እሴቶቹን መጠቀም ለምክክር መድረኩ ስኬታማነት የጎላ ሚና ይጫወታሉ።
ሀገራዊ ምክክር ተጠቅመው ከገቡበት ቀውስ በዘላቂነት በመውጣት የተሻለ ሀገር መገንባት ከቻሉ ከነሩዋንዳና ሌሎችም ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ ተገቢነት አለው። ጽንፈኝነትና አክራሪነት የሚያመጣቸውን መዘዞች ነቅሎ ለመጣል ሁላችንም ልንዘጋጅና የመፍትሄ አካል ከመሆናችን ባሻገር በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የተገነባው አንድነት ይበልጥ ማጠናከር ያስችለናል፡፡
ነገን የተሻለ ለማድረግ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ያደገች፣ የተረጋጋችና ሰላማዊ ሀገር ለመገንባት እና ከምንፈልገው ከፍታ ላይ ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገር ወዳድነት ስሜት የሚችለውን ሁሉ በጎ ሚና መጫወት አለበት።