You are currently viewing የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአገራዊ ብልጽግና እንደርሳለን፤ /በሚራክል እውነቱ/

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ከአገራዊ ብልጽግና እንደርሳለን፤ /በሚራክል እውነቱ/

  • Post comments:0 Comments

አገርም ሆነ ህዝብ ያለ ጠንካራ መንግሥት የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ በሚፈጠር ሁከትና ትርምስ መንግሥት አልባ የሆኑ አገራት የገጠማቸውን ፈተናና መከራ መግለጽም ሆነ መናገር ከሚቻለው በላይ ነው፡፡

ህገ ወጥነትና ስርአት አልበኝነት ሲሰፍን፣ ህግና ስርአት የሚያስከብር ሲጠፋ፣ ለዜጎች ህይወትና ንብረት ዋስትና የሚሆን የለም፡፡ በየዘመኑ መንግሥታት ነበሩን፤ ለዛውም ከማንም በፊት፡፡ በአንድ ወቅት በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ለእንደራሴዎች በሰጡት ምላሽ “አንዳንድ ሀገሮች ከመፈጠራቸው በፊት መንግስት የነበረን ህዝቦች ነን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በህግ የበላይነት ሕግና ስርአትን ማስከበር ካለተቻለና መንግሥት ከሌለ በአገሪቱ ውስጥ በሚፈጠር አለመረጋጋትና ተቃውሞ አጋጣሚውን ለመጠቀም ከውስጥም ሆነ ከውጭ አሰፍስፎ የሚጠብቀው የተደራጀ ዘራፊና ቀማኛ ቡድን ለምንም ነገር ርህራሄና ይቅርታ እንደሌለው የመፍረስና የመበተን አደጋ ገጥሟቸው ከነበሩ በርካታ የአፍሪካ፣ የእስያና የአውሮፓ አገራት ልምድና ተሞክሮ ታይቷል፡፡እኛም ዘንድ ይህ እንዳይሆን አስቀድሞ መጠንቀቅ ለአገርም ለህዝብም ይበጃል፡፡

ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሁናና ተበታትና ከሃያ ሰባት አመታት በላይ ስትዘልቅ ጉልበተኛ የመንደርና የጎበዝ አለቆች የራሳቸውን የታጠቀ ቡድን በየጎጡ አደራጅተው ሲዋጉ ነበር፡፡ አንዱ አንዱን ሲያጠቃ፣ሲገድል፣ሲበድል እና ሲዘርፍ ከዚያም አልፎ የህዝቡ መደበኛና ሰላማዊ ህይወት ሲናጋ፣ መንግሥታዊና ማሀበራዊ ተቋማት ሲፈርሱ፤ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጥፋትና ውድመት ተከስቶ አይተናል፡፡ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ኢራቅን ሊቢያን፣ ሶርያን፣ የመንንና ሌሎችንም በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በትርምስና በእርስ በእርስ መቋሰል ህዝብ የተላለቀበት፣ህግና ስርአት የጠፋበት በእልህና ትንቅንቅ ሀብትና ንብረት የወደመበትን አስከፊ ታሪክ በእኛው ዘመን አይተናል፡፡

የብዙ አገራት የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የህዝብ እልቂትና ስደት መነሻውም ይኸው ነው፡፡መንግሥት የሌላት አገር ካፒቴን እንደሌላት መርከብ ትቆጠራለች ፡፡ ማንም  እንደፈለገው የሚዘውራት ፤ለማንም  ክፍት የሆነች ሀገር ትሆናለች፡፡ ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ ሀይሎች እንዳሉ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ለማየት አይደለም ለመስማት የሚዘገንኑ ድርጊቶች በንጹሃን ዜጎች ላይ ሲፈጸሙ ሰምተናል፤አይተናል፡፡ድርጊቱ እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተፈጸመው? በሚያስብል ደረጃ የጭካኔ ጥግን ተመልክተናል፡፡ አብዛኞቹ በሚባል ደረጃ የሚደርሱ ጥቃቶች በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ሲደርስ የነበረው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን በአፋጣኝ እንዲቆሙ ባይደረግ ኖሮ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ከዚህም በላይ ይሆን ነበር፡፡በእርግጥ ብልጽግና እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግስት ይህንን አይነት የህግ ጥሰት እንዳይደገም ያላሰለሰ ጥረት ከማድረጉም ባሻገር ድርጊቱ እንዲፈጸም ምክንያት የሆኑ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ፓርቲም ሆነ መንግስት ለህዝብ የቆሙ ናቸውና ህዝብን የማዳን ስራ ይሰራል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የአመራሮች እጅ እንዳለበት በተለያዩ ጊዚያት ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ብልጽግና ፓርቲ በዚህ ላይ እጃቸው ያለባቸውን አካላት በአግባቡ በመለየት ከሀላፊነታቸው እንዲነሱና በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ሲሰራ ቆይቷል ፤ይህንኑ እርምጃውንም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ማንም ከህግ በታች እንጂ በላይ ሊሆን አይችልምና፡፡

ህዝብ የአካባቢውን፣የአገሩን ሰላም አጥብቆ ይፈልጋል፤ ለሰላሙም ይቆማል፡፡ሰላም የሁሉም ነገር መነሻ ነውና፡፡ለዚህ ደግሞ እያንዳንዳችን በየአካባቢው ከሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅት ልንሰራ ይገባናል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ ብቻውን ውጤት ማምጣት አይችልም፤ ተገቢውን የህዝብ እገዛ ማግኘት ካልቻለ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አመራሩ ህዝብ የሰጠውን አደራ ወደ ጎን ማድረግና ህዝበኝነት ውስጥ መግባት የሚያስከትለው አደጋ እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ የታሪክ ተወቃሽ መሆንንም ያስከትላል፡፡

ብልጽግና ለህግ የበላይነት መከበር ምንም አይነት ድርድር እንደማያደርግ የራሱን አመራሮች በህግ ተጠያቂ ማድረግ መቻሉ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም ህግ ህግ ነውና፡፡

 

ምላሽ ይስጡ