‹‹የሕግ የበላይነት ማስፈን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል››

‹‹የሕግ የበላይነት ማስፈን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል››

  • Post comments:0 Comments

የህግ የበላይነትን ማስፈን ለድርድር የማይቀርብ የመንግሥት ጽኑ አቋም በመሆኑ አገር ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሣ ገለጹ።

ዶክተር ቢቂላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለድርድር የማይቀርብ የመንግሥት ጽኑ አቋም በመሆኑ አገር ለማፍረስ እየሰሩ ያሉ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ይደረጋል። የሀገሪቱን ሰላም ለማናጋት ብሎም አገር በኃይል ለማፍረስ ሲሰሩ የነበሩና እየሰሩ ያሉ ሕወሓት አመራሮች ሳይቀሩ ሁሉም አጥፊዎች ለህግ የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ጠቁመዋል።

ጽንፈኝነትና አክራሪነት የትኛውንም ብሔር የማይወክል አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ አስተሳሰቡም ሆነ ድርጊቱ የአገር ሁለንተናዊ እንቅቃሴን የሚገታና መዘዙም ህዝብ ላይ የሚከፋ መሆኑን አስገንዝበዋል። በአገሪቱ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ መንግሥት የህልውና ጉዳይ አድርጎ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የአንዳንድ ኃይሎች አገር የማፍረስ ዓላማ ወደፊትም አይሳካም ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ መንግሥት የአገር ህልውና ለመታደግና መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን የህግ የማስከበር እንዲሳካ ህዝቡ የተለመደውን ቀና ትብብር ማድረግ አለበት ብለዋል።

የመንግሥት ትዕግስት እንደ ፍርሃት ተቆጥሮ አገሪቱ በብዙ ችግሮች እንድታልፍ ምክንያት ሆነዋል። ምንም እንኳ የሕወሓት አከርካሪ ቢመታም አሁንም በአንዳንድ አካባቢ ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆናቸው መንግሥት የጀመረው ሕግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው። የተለያዩ ችግሮች በመፍጠር አገርን ለአደጋ ያጋለጡ ሁሉ ለህግ ለማቅረብ በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቁ። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፉት አራት ዓመታት አገሪቱ በሰላም እጦት በእጅጉ ተፈትናለች።

በተለይ አሸባሪው ሕወሓት በአንድ በኩል በአገር ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀን ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውሸት መረጃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምት አድርጓል። የለውጡ አመራርና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል አሸባሪ ቡድኑን በመቅጣት አገር ለመታደግ ተችሏል። ከሕወሓት ሳይማሩ ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉና ጥቅማቸው የተነካባቸው ኃይሎች ከለውጡ ማግስት አንስተው የጥፋት ጎዳናን መርጠዋል። ከአሸባሪው ሕወሓት በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የብሔርና የሃይማኖት አክራሪዎችና ጽንፈኞችም አፋሳሽ እልቂት እንዲፈጠር ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል። በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብሎም ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ምክክር ማድረግ የመንግሥት ጽኑ ፍላጎት ነው። ሁሉም ወገን ለብሄራዊ ምክክሩ ራሱን እንዲያዘጋጅ ጠይቀዋል።

Leave a Reply