አዲስ ብለን የተቀበልነው 2013 ዓ/ም አሮጌ ብለን ልንሸኘው እነሆ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውናል፡፡አዲስ አመትን በአዲስ መንፈስ በብሩህ ተስፋ “አበባ የሆሽ ለምለም” “አበባ የሆሽ ለምለም” በሚል አገርኛ ዜማ ታጅቦ ደረስኩ ደረስኩ በሚልበት እና ዓዲስ ዓመትን ልንቀበል በጣት በቀሩን ቀናት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ለምትኖሩት ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለአዲስ ዓመት በሰላምና በፍቅር አደረሳችሁ ልንል ወደድን፡፡
በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያንዣበበው ጥቁር ደመና ተገፎ የሰላምና የአንድነት አየር የሚንፍስበት ብሎም በአዲሱ ዓመትም የተጀመረው የለውጥ ወጋገን ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ የመላው ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የጋራ ርብርብ ከማስፈለጉም በላይ ብሩህ ዓመት ሆኖ እንቀበለው ዘንድ የጋራ አንድነታችንን አጠናክረን በወንድማማችነት ስሜት በፍቅር ተዛምድን ነጋችንን በብርሀን ፍንጣቂ ለማድመቅ የጋራ ተነሳሽነታችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
በብልጽግና ዘመን የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ከዚህም በላይ በአግባቡ ለማጣጣም አስተዋይነትን ይፈልጋል፡፡ ሀገራችን በበርካታ ሀገራዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ተከባ ነው ያለችው፡፡
ከከበባት ተግዳሮቶች ለማውጣት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ልንቆም ያስፈልጋል፡፡ምዕራባዊያን ከአገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው ጋር በመሆን በአገር ላይ ጫና ለመፍጠር በሚረባረቡበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያን የአንድነት ድምጻችንን ማሰማት የግድ ሆኗል፡፡
አንድነታችን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ብርታት ለጠላቶቻችን ደግሞ ፍርሃትን ይፈጥራል፡፡የውስጥና የውጭ ሀይሎችን ጫና ተቋቁመን የምንፈልገውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ዛሬ ላይ በተደራጀ መንገድ አንድነታችንን ልናሳይ ይገባል፡፡