በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች 15 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር እየተከናወነ ይገኛል
“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መርህ በሀገር ደረጃ የተጀመረው መርሐ ግብር አካል የሆነው እና የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የተገኙበት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሲዳማ ክልል ጋራ ሪቂታ ቀበሌ ቡርቂቶ ኢባሊቾ መንደር ተከናወነ።
በችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ላይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ፣የክልሉ ም/ፕሬዚዳንትና የት/ት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንዲሁም የክልሉ ካቢኔ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ተከናውኗል።
በመርሀ ግብሩም ላይ በመገኘት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት ችግኞችን መትከላችን አካባቢያችንን ከተፈጥሮ መዛባትን በመጠበቅ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደሚያበረክቱ በመግለጽ በዛሬው ዕለት በመላው የክልሉ አካባቢዎች ህብረተሰቡ በነቂስ በመውጣት 15 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል ።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው በከተማው በሁሉም ክፍለ ከተሞች በዛሬው መርሐ ግብር 500,000 ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩም ላይ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ችግኝ ተከላውን አከናውነዋል።