/በሚራክል እውነቱ/
የፖለቲካ ምርጫ ህዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጥበትና ለዚህም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት አካል ነው፡፡ ሂደቱ የሚከናወነውም ሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዘጋጀላቸው እኩል መድረክ ተወዳድረው አማራጫቸውን ለህዝቡ በማቅረብ የመንግስት ስልጣን ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡
ኢትዮጵያም የፖለቲካ ምርጫን ከጀመረች የቆየች ቢሆንም፤እስካሁን በህዝቡ ተቀባይነትና መተማመን ላይ የደረሰ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውጤት ላይ ለስልጣን የበቃ የመንግስት ስርዓት ለማየት እንዳልተቻለ ይነገራል፡፡
የፖለቲካ ምርጫ ዓላማ፣ጠቀሜታና አስፈላጊነት ዜጎችን የሀገራቸው ስልጣን ባለቤት ከማድረግ ጎን ለጎን ሀገሪቱን የመምራት ዕድል ባጋጠማቸውና በህዝቡ መካከል መተማመን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው የነቃ ተሳትፎ የሚደርስባቸውን ግድያ፣ እስር፣ ስቃይ፣ ስደት፣አድሎና መገለልን ለማጥፋትና ለመቀነስም ይረዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ ነው የቆየው ማለት ይቻላል፡፡
ምክንያቱም የፖለቲካ ስልጣን ምርጫ በቀረበ ቁጥር መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ዜጎች ላይ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ተባብሶ የሚቀጥል በመሆኑ፤በገዥው ስርዓት በሚወሰዱ ወታደራዊ የኃይል እርምጃዎች መቀነስ ሲገባቸው ይበልጥ ተጠናክረው በመቀጠል በርካታ ንፁሃን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ፡፡
በሚፈጠሩ ስህተቶችም የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ሆኑ አዛዦቹ ኃላፊነት ወስደው አያውቁም፤ ሲወስዱም አይታይም፡፡ምርጫ በቀረበ ቁጥር ሌላው የሚስተዋለው ችግር የፍትህ ስርዓቱ በህዝብ ያለው ተቀባይነትና አመኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡
በተለይም ከገዥው ስርዓት ተቃራኒ ሐሳብ ያነሱት ላይ የሚመሰረተው ክስ፣ የፍርድ ሂደት እጅግ መዘግየትና ፍርዱ ምርጫ ሲመጣ ከመቼውም ቀናት በላቀ ፍርሃት ሲነግስበት ይታያል፡፡ ይሄ በገዥውም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በህዝቡ የሚስተዋል አውነታ ነው፡፡
ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በስልጣን ላይ ያለው አካል የራስ መተማመን ያለመኖርና የህዝብ አመኔታና ቅቡልነት አለኝ ብሎ ባለማመኑ በሚፈጠር ፍርሃት ነው በሚል ብዙዎች ሲተቹት ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ምርጫ ሲቀርብና ሲመጣ ከበጎ ጎን ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹ ጎልተው ይወጣሉ፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ዘንድሮ ማለትም በ2013 ስለሚካሄደው ምርጫ አስመልክቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ምርጫው በህዝቡ ዘንድ ፍጹም ተአማኒነትን ያተረፈ፣ነጻና ፍተሃዊ ምርጫ ለማስኬድ እንዲሁም በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ፓርቲው ያለውን ቁርጠኝነት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
እርግጥ ነው ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ ዜጎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው የነቃ ተሳትፎ ምክንያት የሚደርስባቸው ግድያም ሆነ እስር፣ ስቃይም ሆነ ስደት፣አድሎም ሆነ መገለል ሊኖር አይችልም፤ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችል የፍትህ ስርዓት ጉድለት እንዳይኖር ፓርቲው አበክሮ እየሰራ ይገኛል፤ በተግባር የሚታይ ሀቅ ነው፡፡
በህብር ወደ ብልጽግና !