በአማራ ክልል የተካሄደው የምዕራብና የሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ፤

በአማራ ክልል የተካሄደው የምዕራብና የሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ፤

  • Post comments:0 Comments

በፌደሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት “መልካም ጉርብትና ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የነበረው የምዕራብና ሰሜን ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የጋራ ምክክር መድረክ ተጠናቀቀ።

በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ አዲሱን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጨምሮ ከስድስት በላይ የተጎራባች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና አፈ ጉባኤዎች የተሳተፉ ሲሆን “በህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርዓት የክልሎች የርስ በርስ ግንኙነት ስርዓት አስፈላጊነት” በሚል ርዕስ መነሻ ፅሁፍ ቀርቦ በቀረበው ፅሁፍ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ተጠናቋል።

የውይይት መድረኩ ዋንኛ ዓላማ አድርጎ የነበረው እውነተኛ የፌደራል ስርዓት በመገንባት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ለዚህም ክልሎች በሰላም፣ በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ በሕግ የበላይነትና በሰብዓዊ መብት መከበር የተቀራረበ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

ስለ ፌደራሊዝም ስርዓት አወቃቀር የስዊዘርላንድና የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ ቀርቦ ከኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት አወቃቀር ጋር ተገናዝቦ ውይይት ተደርጎ ሀሳብ ተሰጥቶበታል። በውይይቱ ላይ የፌደራል ስርዓቱ ከአመሰራረቱ እና ከአተገባበሩ ጀምሮ ችግር ያለበት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን አንዱን ያነሰ አንዱን ደግሞ አናሳ በሚል እና ከፍ ያለ የሚለውንም ቢሆን ጠባብና ትምክተኛ የሚል ታርጋ ለጥፎ ሲተገበር የነበረ እንደነበር ተሳታፊዎቹ በመግለፅ አሁን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ እኩል የሚሳተፍበትና የሚወስንበት ዕድል በመፈጠሩ ይህን በማጠናከር ለህዝቦች የጋራ ጥቅም መስራት አለብን ሲሉ አንስተዋል።

ስለሆነም እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት መጀመሪያ የአስተሳሰብ ግንባታ ስራ መሰራት እንዳለበት በስፋት የተነሳ ሲሆን የአስተሳሰብ ግንባታ ስራ ለመስራት ደግሞ መሪዎች ቁርጠኛ ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባም ተገልጿል።

የትኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ቢኖር እንደማንኛውም ዜጋ እኩል መብቱና ሰላሙ ተጠብቆ ሊኖር እንደሚገባም የተነሳ ሲሆን ይህ እንዲሆንም ከላይ እስከታች ያለው መሪ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለበት፤ የአስተሳሰብ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ የአሰራር ለውጥ ቢደረግም ችግሩ ሊቀረፍ እንደማችል በአፅንኦት ተነስቷል።

ስለሆነም የክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ የጋራ የሆኑ ስራዎችን ለይተው በጋራ እንዲያቅዱና በጋራ እንዲፈፅሙ በውይይቱ ላይ የተመላከተ ሲህን መሪዎች ከግል እሳቤና ፍላጎታቸው ወጥተው ተህዝቦች ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም እድገት መስራት እንዳለባቸው እና መሪዎቹ በአስተሳሰብ ተለውጠው እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓትን ገንብተው የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው ከሰሩ በህዝቦች ዘንድ ከፍተኛ እምነት እንደሚያገኙም ነው የተገለፀው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዜጎች በማንነታቸው ብቻ እየተመረጡ በግፍ ሲጨፈጨፉና ሲፈናቀሉ ችግሩ ቀድሞ እንዳይከሰት ከመስራት ባለፈ ከተከሰተም በኋላ ፈጥኖ ችግሩን ያልቀረፈ የክልል መሪ በዚህ ተግባሩ እራሱ ሊያፍር እንደሚገባውና ከዚህ ችግር ለመውጣትም በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ የፌደሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ በማጠቃለያ ሀሳባቸው ገልፀዋል።

አቶ አደም ፋራህ አያይዘውም ዓላማውን ለማሳካትና በሂደቱ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር የጋራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የጋራ የአመራር ብቃት መገንባት እንደሚያስፈልግ የገለፁ ሲሆን ክልሎች ከዚህ ችግር ለመውጣትና የውይይቱ ዓላማ ግብ መትቶ ለውጥ ለማምጣት የየክልሎች አፈ ጉባኤዎች ፎካል ፐርሰን በመሆን የክልሎችን የጎንዮሽ የጋራ የምክክር መድረክ እየተከታተሉ ለውጡን እንዲገመግሙ ተወክለዋል።

በመድረኩ ላይ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን በተመለከተ ሀሳብ የተነሳ ሲሆን የህዝቦችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በህግ አግባብ ምላሽ እንደሚሰጥ የማጠቃለያ ሀሳብ ተሰጥቷል።

በማጠቃለያ ሀሳቡ ላይ እንደ ትህነግ/ወያኔ የህዝቦችን መብት ማፈን እንደማይቻል የተነሳ ሲሆን ምርጫውን ለህዝቦች ሰጥቶ በህዝቦች ፍላጎት ምላሽ ኤየሰጡ ለአንድነትና ለጋራ ጥቅም ግን በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ጭምር ተነስቷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ስለ ሀገ-መንግስቱ መሻሻል የተነሳ ሲሆን ትህነግ/ወያኔ የሀሰት ትርክት የተሞላበት ህገ-መንግስት አዘጋጅታ እኛ እና እነርሱ በሚል ነጣጣይ ሀሳብ እየተጓዘ የጥላቻ መርዝ በመርጨት በዜጎች ላይ በርካታ ግፍ ሲፈፅም ቆይቷል፤ አሁንም ትህነግ/ወያኔ የዘራው የጥላቻ ትርክት ተነቅሎ አልጠፋም፤ ይህ የተሳሳተና ህዝቦችን በጥርጣሬ እያሳዬ ሲያባላ የነበረ ትረሰክት መነቀል አለበት ሲሉ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ስለ ህገ-መንግስቱ መሻሻል የማጠቃለያ ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን ህገ-መንግስቱ የማይሻሻልበት መንገድ የለም፤ አሁን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን እና ወደ ፊትም የምትደርስበትን ታሳቢ በማድረግ ህገ መንግስቱ ሊሻሻል ይችላል። ለዚህ ደግሞ በየ ደረጃው ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልግ ነው የተገለፀው።

በመጨረሻም “ኢትዮጵያን የሚመጥን ስራ መስራት አለብን፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን ስራ ካልሰራን እንጠፋለን፣ ኢትዮጵያን የማይመጥን ስራ የሰሩ ሁሉ ጠፍተዋል” የሚል ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ሞት እንዲሁም መፈናቀል ያለባት ሀገር ናት፤ ይህን ለማስቀረት ኢትዮጵያን የሚመጥን ስራ መስራት እንደሚገባም ነው በመድረኩ ላይ ተገልፆ የተጠናቀቀው።

Leave a Reply